2 ነገሥት 3:1-27

2 ነገሥት 3:1-27 NASV

የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በእስራኤል ላይ በሰማርያ ነገሠ፤ ዐሥራ ሁለት ዓመትም ገዛ። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ ክፉ ድርጊቱ ግን አባትና እናቱ እንደ ፈጸሙት ዐይነት አልነበረም፤ አባቱ ያሠራውንም የበኣልን ሐውልት አስወገደ። ነገር ግን የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ባሳተበት ኀጢአት ተያዘ፤ ከዚያም አልተላቀቀም። በዚህ ጊዜ የሞዓብ ንጉሥ ሞሳ በግ ያረባ ነበር፤ እርሱም መቶ ሺሕ ጠቦትና የመቶ ሺሕ አውራ በግ ጠጕር ለእስራኤል ንጉሥ ይገብር ነበር። አክዓብ ከሞተ በኋላ ግን የሞዓብ ንጉሥ በእስራኤል ንጉሥ ላይ ዐመፀ። ስለዚህ በዚያ ጊዜ ንጉሥ ኢዮራም ከሰማርያ ተነሥቶ በመሄድ እስራኤልን ሁሉ አሰባሰበ። ለይሁዳ ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “የሞዓብ ንጉሥ ስለ ዐመፀብኝ ዐብረኸኝ ትዘምታለህን?” ሲል መልእክት ላከበት። እርሱም፣ “አዎን ዐብሬህ እዘምታለሁ፤ እኔ እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤ እንደ ሕዝብህ፤ ፈረሶቼም እንደ ፈረሶችህ ናቸው” በማለት መለሰለት። ኢዮሣፍጥም፣ “የምንዘምተው በየትኛው መንገድ ነው” ብሎ ጠየቀው። ኢዮራምም “በኤዶም ምድረ በዳ ዐልፈን ነው” ሲል መለሰለት። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከይሁዳ ንጉሥና ከኤዶም ንጉሥ ጋራ ለመዝመት ተነሣ። ሰባት ቀን ከዞሩም በኋላ ለሰራዊቱም ሆነ ለእንስሶቻቸው የተረፈ ውሃ አልነበረም። የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ወዮ! እግዚአብሔር እኛን ሦስት ነገሥታት የጠራን ለሞዓብ አሳልፎ ሊሰጠን ነውን?” አለ። ኢዮሣፍጥ ግን፣ “በርሱ አማካይነት እግዚአብሔርን ለመጠየቅ እንድንችል፣ የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” በማለት ጠየቀ። ከእስራኤል ንጉሥ የጦር አለቆችም አንዱ፣ “ቀድሞ የኤልያስን እጅ ያስታጥብ የነበረው፤ የሣፋጥ ልጅ ኤልሳዕ በዚህ አለ” ብሎ መለሰለት። ኢዮሣፍጥም፣ “የእግዚአብሔር ቃል ከርሱ ዘንድ ይገኛል” አለ፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ፣ ኢዮሣፍጥና የኤዶም ንጉሥ ዐብረው ወደ እርሱ ወረዱ። ኤልሳዕም የእስራኤልን ንጉሥ፤ “ከአንተ ጋራ ምን የሚያገናኘን ጕዳይ አለና መጣህ፤ አሁን የአባትህና የእናትህ ነቢያት ወዳሉበት ሂድ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ መልሶ፣ “ይህማ አይሆንም፤ በሞዓብ እጅ አሳልፎ ሊሰጠን እኛን ሦስት ነገሥታት አንድ ላይ የጠራን እግዚአብሔር ነው” አለ። ኤልሳዕም እንዲህ አለው፤ “የማገለግለው የሰራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔርን፣ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባላከብር ኖሮ፣ አንተን አላይም ወይም ጕዳዬ አልልህም ነበር። አሁንም ባለበገና አምጡልኝ።” ታዲያ ባለበገናው በሚደረድርበት ጊዜ፣ የእግዚአብሔር እጅ በኤልሳዕ ላይ መጣ፤ እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር የሚለው እንዲህ ነው፤ ‘በዚህ ሸለቆ ብዙ ጕድጓዶች ቈፍሩ።’ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ ‘ነፋስም ሆነ ዝናብ አታዩም፤ ሸለቆው ግን በውሃ ይሞላል፤ እናንተ፣ የቀንድ ከብቶቻችሁና ሌሎች እንስሶቻችሁም ትጠጣላችሁ።’ ይህ በእግዚአብሔር ፊት ቀላል ነገር ነው። ሞዓብንም በእጃችሁ አሳልፎ ይሰጣችኋል። የተመሸጉትን ከተሞችና ያማሩትን ከተሞቻቸውን ሁሉ ድል ታደርጋላችሁ። ውብ ዛፎቻቸውን ሁሉ ትቈርጣላችሁ፤ ምንጮቻቸውን በሙሉ ትደፍናላችሁ፤ መልካሙንም ዕርሻ በድንጋይ ታበላሹታላችሁ።” በማግስቱም መሥዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ፣ እነሆ፤ ከኤዶም በኩል ውሃ እየጐረፈ መጣ፤ ምድሪቱም ውሃ በውሃ ሆነች። በዚህ ጊዜ ነገሥታቱ ሊወጓቸው መምጣታቸውን ሞዓባውያን ሁሉ ሰምተው ነበርና፣ ልጅም ሆነ ሽማግሌ፣ መሣሪያ መያዝ የቻለ ሁሉ ተጠርቶ በመውጣት በጠረፉ ላይ ይጠባበቅ ጀመር። በማግስቱም ጧት ማልደው ሲነሡም፣ ፀሓይ በውሃው ላይ ታንጸባርቅ ነበር። ማዶ ላሉት ሞዓባውያንም፣ ውሃው እንደ ደም ቀልቶ ታያቸው። ስለዚህ፣ “ያ እኮ ደም ነው! ያለ ጥርጥር ነገሥታቱ እርስ በርስ ተዋግተው ተራርደዋል። እንግዲህ ሞዓብ ወደ ምርኮህ ዙር!” ተባባሉ። ሞዓባውያን ወደ እስራኤል ሰፈር ሲወጡም፣ እስራኤላውያን ተነሥተው ወጓቸው፤ ሞዓባውያንም ከፊታቸው ሸሹ። ከዚያም እስራኤላውያን ምድሪቱን ወርረው ሞዓባውያንን ፈጇቸው። ከተሞቹን ደመሰሱ፤ መልካሙን የዕርሻ መሬት ሁሉ እስኪሸፍነው ድረስ፣ እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ ድንጋይ ጣለበት፤ ምንጮቹን በሙሉ ደፈኑ፤ ጥሩ ጥሩውንም ዛፍ ሁሉ ቈርጠው ጣሉ። ቂርሐራሴት ብቻ ከነድንጋይዋ ቀርታ ነበር፤ እርሷንም ቢሆን ባለወንጭፉ ሰራዊት ከብቦ አደጋ ጣለባት። የሞዓባውያን ንጉሥ በጦርነቱ መሸነፉን እንዳወቀ፣ ሰይፍ የታጠቁ ሰባት መቶ ሰዎች ይዞ የኤዶም ንጉሥ ወዳለበት ጥሶ ለመግባት ሞከረ፤ ነገር ግን አልተሳካላቸውም። ከዚያም በእግሩ ተተክቶ የሚነግሠውን፣ የበኵር ልጁን ወስዶ በከተማዪቱ ቅጥር ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው። በእስራኤልም ላይ ታላቅ ቍጣ ሆነ፤ ከዚያም ለቅቀው ወደ ገዛ ምድራቸው ተመለሱ።