2 ነገሥት 24:8-20

2 ነገሥት 24:8-20 NASV

ዮአኪን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሦስት ወር ገዛ። እናቱ ኔስታ ትባላለች፤ እርሷም የኢየሩሳሌም ሰው የኤልናታን ልጅ ነበረች። አባቱ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። በዚያ ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነፆር ጦር አለቆች ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ መጥተው ከበቧት፤ የጦር አለቆቹ ከበባ በሚያደርጉበትም ሰዓት ንጉሥ ናቡከደነፆር ራሱ ወደ ከተማዪቱ መጣ። የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን፣ እናቱ፣ የክብር አጃቢዎቹ፣ መሳፍንቱና ሹማምቱ ሁሉ እጃቸውን ለባቢሎን ንጉሥ ሰጡ። የባቢሎን ንጉሥ በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ዮአኪንን ማርኮ ወሰደው። እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደ ተናገረው፣ ናቡከደነፆር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና የቤተ መንግሥቱን ሀብት በሙሉ አጋዘ፤ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያሠራቸውንም የወርቅ ዕቃዎች ሁሉ ወሰደ። ደግሞም የኢየሩሳሌምን ሕዝብ እንዳለ የጦር አለቆቹንና ተዋጊዎቹን በሙሉ፣ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ቀጥቃጮችን ሁሉ ጨምሮ በአጠቃላይ ዐሥር ሺሕ ሰው በምርኮ ወደ አገሩ ወሰደ። በዚያ የቀሩት የመጨረሻዎቹ ያገሪቱ ድኾች ብቻ ነበሩ። ናቡከደነፆር ዮአኪንን ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ እንዲሁም የንጉሡን እናት፣ ሚስቶቹን፣ ሹማምቱና በአገር የታወቁትን ታላላቅ ሰዎችም ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ወሰደ። ደግሞም የባቢሎን ንጉሥ በአጠቃላይ ብርቱ የሆኑትንና ለጦርነት ብቃት ያላቸውን ሰባት ሺሕ ተዋጊዎች፣ አንድ ሺሕ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ቀጥቃጮችን በምርኮ ወደ ባቢሎን ወሰደ። ከዚያም የዮአኪንን አጎት ማታንያን በምትኩ አነገሠው፤ ስሙንም ሴዴቅያስ ብሎ ለወጠው። ሴዴቅያስ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ አንድ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ። የእናቱም ስም አሚጣል ነበረ፤ እርሷም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። ኢዮአቄም እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ። እንግዲህ ይህ ሁሉ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሊደርስ የቻለው ከእግዚአብሔር ቍጣ የተነሣ ነበር፤ በመጨረሻም ከፊቱ አስወገዳቸው።