2 ነገሥት 23:1-27

2 ነገሥት 23:1-27 NASV

ከዚያም ንጉሡ ልኮ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች በአንድ ላይ ሰበሰበ። ንጉሡም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ፣ የኢየሩሳሌምን ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ፣ ካህናቱንና ነቢያቱን ሁሉ ከልጅ እስከ ዐዋቂ አንድም ሰው ሳይቀር ይዞ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጣ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተገኘውንም የኪዳኑን መጽሐፍ ቃል በሙሉ በጆሯቸው እንዲሰሙት አነበበላቸው። ንጉሡም በዐምዱ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ እግዚአብሔርን እንደሚከተል ትእዛዞቹን፣ ደንቦቹን፣ ሥርዐቶቹን በፍጹም ልቡና በፍጹምም ነፍሱ እንደሚጠብቅ፣ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን ኪዳን እንደሚያጸና በእግዚአብሔር ፊት ኪዳኑን አደሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ ቃል ኪዳን ገቡ። ንጉሡም ለበኣል፣ ለአሼራና ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊት ሁሉ የተሠሩትን የመገልገያ ዕቃዎች በሙሉ፣ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲያወጡ ሊቀ ካህናቱን ኬልቅያስን በሁለተኛ ማዕርግ ያሉትን ካህናትና የቤተ መቅደሱን በር ጠባቂዎች አዘዘ። ዕቃዎቹንም ከኢየሩሳሌም ውጭ በቄድሮን ሸለቆ ሜዳ ላይ አቃጠላቸው፤ ዐመዱንም ወደ ቤቴል ወሰደው። በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም ዙሪያ በሚገኙ ኰረብቶች ላይ ዕጣን እንዲያጥኑ የይሁዳ ነገሥታት የሾሟቸውን የጣዖት ካህናት አባረረ እንዲሁም ለበኣል፣ ለፀሓይና ለጨረቃ፣ ለስብስብ ከዋክብትና ለመላው የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት የሚያጥኑትን አስወገደ። የአሼራንም ምስል ዐምድ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አውጥቶ ከኢየሩሳሌም ውጭ ወዳለው ወደ ቄድሮን ሸለቆ ወስዶ አቃጠለው፤ አድቅቆ ፈጭቶም በሕዝቡ መቃብር ላይ በተነው። እንዲሁም ስለ አምልኮ ባዕድ ሥርዐት በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የቤተ ጣዖት ወንደቃዎችን ክፍሎችና ሴቶች ለአሼራ መጋረጃ የሚፈትሉባቸውን ክፍሎች አፈረሰ። ኢዮስያስ የቤተ ጣዖት ካህናትን ሁሉ ከይሁዳ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም አወጣቸው፤ ከጌባዕ ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ፣ ካህናቱ ዕጣን ያጥኑባቸው የነበሩትን የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራዎችን አረከሰ። ከከተማዪቱ በር በስተግራ በኩል፣ በከተማዪቱ ገዥ በኢያሱ በር መግቢያ አጠገብ የነበሩትን የበሮቹን ማምለኪያ ስፍራዎች አፈረሰ። የየኰረብታው ማምለኪያ ካህናት ኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ባያገለግሉም እንኳ ከካህናት ወንድሞቻቸው ጋራ ቂጣ ይበሉ ነበር። በሄኖም ሸለቆ የነበረውን ቶፌት የተባለውን ማምለኪያ አረከሰ፤ ይኸውም ማንም ሰው ወንድ ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ እንዳያቀርብበት ነው። የይሁዳ ነገሥታት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግቢያ ላይ ለፀሓይ አምልኮ የሰጧቸውን ፈረሶች ከዚያ አስወገደ። እነዚህም ናታን ሜሌክ በተባለ በአንድ ሹም ቤት አጠገብ በአደባባዩ ላይ ነበሩ። ኢዮስያስም ለፀሓይ አምልኮ የተሰጡትን ሠረገሎች አቃጠለ። የይሁዳ ነገሥታት በላይኛው የአካዝ እልፍኝ አጠገብ በሰገነቱ ላይ ያቆሟቸውን መሠዊያዎች፣ ምናሴም በሁለቱ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ላይ ያሠራቸውን መሠዊያዎች አስወገደ፤ ስብርብራቸውን አወጣ፤ ድቃቂውንም አንሥቶ ወደ ቄድሮን ሸለቆ ጣለው። እንዲሁም ከኢየሩሳሌም በስተምሥራቅ ከርኩሰት ኰረብታ በስተ ደቡብ የነበሩትን የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለሲዶናውያን የርኩሰት አምላክ ለአስታሮት፣ ለሞዓብ ሕዝቦች የርኩሰት አምላክ ለካሞሽ፣ ለአሞን ሕዝቦች የርኩሰት አምላክ ለሚልኮም ያሠራቸውን የኰረብታ ላይ ማምለኪያዎች ንጉሡ አረከሰ። አሁንም ኢዮስያስ ማምለኪያ የድንጋይ ሐውልቶችን ሰባበረ፤ የአሼራን ምስል ዐምዶች ቈራረጠ፤ ስፍራውንም በሞቱ ሰዎች ዐጥንት ሞላው። እስራኤልን ባሳተው በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም የተሠራውን መሠዊያ፣ በቤቴል የነበረውን ያን የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራ፣ መሠዊያው ያለበትን ያን የኰረብታ ማምለኪያ ስፍራ እንኳ እንደዚሁ አፈረሰ፤ ድንጋዮቹን ሰባበረ፤ እንደ ዱቄትም አደቀቃቸው፤ የአሼራንም ምስል ዐምድ አቃጠለ። ኢዮስያስ ዘወር ሲል በኰረብታው ላይ የነበሩትን መቃብሮች አየ፤ ዐፅሞቹንም ከየመቃብሩ አስወጣ፤ ያ የእግዚአብሔር ሰው አስቀድሞ እንደ ተናገረው፣ የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ መሠዊያውን ለማርከስ ሲል ዐፅሞቹን በላዩ ላይ አቃጠለበት። ንጉሡም፣ “ያ የማየው የመቃብር ሐውልት የማን ነው?” ሲል ጠየቀ። የከተማዪቱም ሰዎች፣ “ከይሁዳ መጥቶ አሁን አንተ ያደረግኸውን ነገር ሁሉ በቤቴል መሠዊያ ላይ እንደሚደርስ የተናገረ የዚያ የእግዚአብሔር ሰው መቃብር ነው” አሉት። ኢዮስያስም፣ “በሉ እንዳለ ተዉት፤ ዐፅሙን ማንም ሰው ከቦታው እንዳያንቀሳቅሰው” አለ፤ ስለዚህ የእርሱንና ከሰማርያ የመጣውን ነቢይ ዐፅም ሳይነኩ እንዳለ ተውት። ኢዮስያስም በቤቴል እንዳደረገው ሁሉ በሰማርያም ከተሞች ኰረብቶች ላይ የእስራኤል ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትንና እግዚአብሔርን ያስቈጡበትን ቤተ ጣዖቶች ሁሉ አስወገደ፤ አረከሳቸውም። ኢዮስያስ እነዚያን የየኰረብታውን ማምለኪያ ቦታ ካህናትን ሁሉ፣ በየመሠዊያው ላይ ዐረዳቸው፤ በመሠዊያዎቹ ላይ የሰው ዐፅም አቃጠለ፣ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። ንጉሡም መላውን ሕዝብ፣ “በዚህ በኪዳኑ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ፋሲካ አክብሩ” ብሎ አዘዘ። እስራኤልን ከመሩ ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ፣ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ፣ እንደዚህ ያለ ፋሲካ መቼም ተከብሮ አያውቅም። በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ግን ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ተከበረ። ከዚህም በቀር ኢዮስያስ ሙታን አነጋጋሪዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን፣ የየቤተ ሰቡ ሰውን አማልክት፣ ጣዖታትን እንዲሁም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የተገኙትን ሌሎች አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ አስወገደ፤ ይህን ያደረገውም ካህኑ ኬልቅያስ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ባገኘው መጽሐፍ የተጻፈው የሕጉ ቃል ተፈጻሚነት እንዲኖረው ለማድረግ ነው። በሙሴ ሕግ በተጻፈው መሠረት በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም ነፍሱ፣ በፍጹም ኀይሉ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ፣ እንደ ኢዮስያስ ያለ ንጉሥ፣ ከርሱ በፊትም ሆነ ከርሱ በኋላ ፈጽሞ አልተነሣም። ይህም ሆኖ እንኳ ለቍጣ እንዲነሣሣ ምናሴ ካደረጋቸው ነገሮች ሁሉ የተነሣ፣ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ከነደደው ከአስፈሪው ቍጣው ገና አልበረደም ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር፣ “እስራኤልን እንዳስወገድሁ ሁሉ ይሁዳንም ከፊቴ አስወግዳለሁ፤ የመረጥኋትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና፣ ‘ስሜ በዚያ ይሆናል’ ብዬ የተናገርሁለትን ይህን ቤተ መቅደስ እተዋለሁ” አለ።