2 ነገሥት 21:1-16

2 ነገሥት 21:1-16 NASV

ምናሴ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐምሳ ዐምስት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ሐፍሴባ ትባል ነበር። እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት አሳድዶ ያስወጣቸውን የአሕዛብን አስጸያፊ ልማድ በመከተል በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። አባቱ ሕዝቅያስ የደመሰሳቸውን የኰረብታ ላይ ማምለኪያ ስፍራዎች መልሶ ሠራ፤ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም ለበኣል መሠዊያዎችን አቆመ፤ የአሼራንም ምስል ዐምዶች ሠራ። እንዲሁም ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊትም ሁሉ ሰገደ፤ አመለካቸውም። እግዚአብሔር፣ “ስሜን በኢየሩሳሌም አኖራለሁ” ባለበት በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠዊያዎችን ሠራ። በሁለቱም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባዮች ለሁሉም የሰማይ ከዋክብት ሰራዊት መሠዊያዎችን ሠራ። የገዛ ወንድ ልጁን በእሳት ሠዋ፤ አስማት፣ መተትና ጥንቈላ አደረገ፤ ሙታን ጠሪዎችንና መናፍስት ሳቢዎችን ጠየቀ። ለቍጣ ያነሣሣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ክፉ ነገር አደረገ። ያበጀውን የአሼራን የተቀረጸ ምስል ወስዶ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አስቀመጠ፤ ይህም እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን፣ “በዚህ ቤተ መቅደስና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ” ያለው ስፍራ ነው። እንዲሁም፣ “ብቻ ያዘዝኋቸውን ሁሉ ተጠንቅቀው በመፈጸምና ባሪያዬ ሙሴ የሰጣቸውንም ሕግ በሙሉ በመጠበቅ ይጽኑ እንጂ ከእንግዲህ የእስራኤላውያን እግር፣ ለአባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ምድር ወጥቶ እንዲንከራተት አላደርግም” ያለው ስለዚሁ ስፍራ ነው። ሕዝቡ ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ የባሰ ክፉ ድርጊት እንዲፈጽሙ ምናሴ አሳታቸው። እግዚአብሔር በባሪያዎቹ በነቢያት አማካይነት እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ሁሉ አስጸያፊ ኀጢአት ሠርቷል፤ ከርሱ በፊት ከነበሩት አሞራውያን ይልቅ ክፉ ድርጊት ፈጽሟል፤ ይሁዳንም በጣዖታቱ አስቷል። ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘ለሚሰማ ሁሉ ጆሮዎቹ ጭው እንዲሉ የሚያደርግ ክፉ መከራ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ። በሰማርያ ላይ ያዘጋጀሁትን መለኪያ ገመድ፣ የአክዓብንም ቤት የለካሁበትን ቱንቢ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ፤ አንድ ሰው ሳሕን እንደሚወለውል ከወለወለም በኋላ እንደሚገለብጠው እኔም ኢየሩሳሌምን ወልውዬ እገለብጣታለሁ። የርስቴንም ቅሬታ እተዋቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ብዝበዛና ምርኮ ይሆናሉ። ይህን የማደርገውም የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብጽ ምድር ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ድርጊት ስለ ፈጸሙና ለቍጣ ስላነሣሡኝ ነው።’ ” ይልቁንም ምናሴ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት እንዲፈጽም ይሁዳን ካሳተበት ኀጢአት ሌላ፣ ኢየሩሳሌምን ከዳር እስከ ዳር እስኪሞላት ድረስ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ።