2 ነገሥት 19:29-35

2 ነገሥት 19:29-35 NASV

“ሕዝቅያስ ሆይ፤ ምልክቱ ይህ ነው፤ “በዚህ ዓመት በገዛ እጁ የበቀለውን፣ በሚመጣው ዓመት ደግሞ የገቦውን እህል ትበላላችሁ፤ በሦስተኛው ዓመት ግን ትዘራላችሁ፤ ታጭዳላችሁ፤ ወይንም ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ። አሁንም ከይሁዳ ቤት የተረፉት፣ ሥራቸውን ወደ ታች ይሰድዳሉ፤ ወደ ላይም ፍሬ ያፈራሉ። ቅሬታ የሆኑት ከኢየሩሳሌም፣ የተረፉትም ከጽዮን ተራራ ይመጣሉና። የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቅናት ይህን ያደርጋል። “ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤ “ ‘ወደዚህች ከተማ ፈጽሞ አይገባም፤ ፍላጻም አይወረውርባትም፤ ጋሻ አንግቦ አይቀርብም፤ በዐፈርም ቍልል አይከብባትም። በመጣበት መንገድ ይመለሳል፤ ወደዚህች ከተማም አይገባም’ ይላል እግዚአብሔር። ‘ስለ ራሴና ስለ ባሪያዬ ስለ ዳዊት ስል፣ ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ፤ አድናታለሁም።’ ” በዚያችም ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ ወጣ፤ ከአሦራውያን ሰፈር አንድ መቶ ሰማንያ ዐምስት ሺሕ ሰው ገደለ፤ ሰዎቹ ማለዳ ሲነሡ፤ ቦታው ሬሳ በሬሳ ነበር።