ሕዝቅያስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ የእስራኤልም ንጉሥ የኤላ ልጅ ሆሴዕ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር ወደ ሰማርያ ገሥግሦ ከተማዪቱን ከበባት፤ በሦስተኛውም ዓመት መጨረሻ ያዛት። ሰማርያ የተያዘችውም ሕዝቅያስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት፣ ሆሴዕ በእስራኤል ላይ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት ነበር። የአሦር ንጉሥ እስራኤልን ማርኮ ወደ አሦር በማፍለስ በአላሔ፣ በጎዛን ውስጥ በአቦር ወንዝ አጠገብና በማዴ ከተሞች አሰፈራቸው። ይህ የደረሰባቸውም የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዘውን የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመስማት ይልቅ ኪዳኑን ስላፈረሱ ነበር፤ ትእዛዞቹን አላደመጡም፤ ደግሞም አልፈጸሙም። ንጉሥ ሕዝቅያስ በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፣ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም የተመሸጉትን የይሁዳ ከተሞች ሁሉ አጥቅቶ ያዛቸው። ስለዚህ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ “በደለኛው እኔ ነኝ፤ ተመለስልኝ፤ እኔም የምትጠይቀኝን ሁሉ እከፍላለሁ፤” ሲል በለኪሶ ወደ ሰፈረው ወደ አሦር ንጉሥ ይህን መልእክት ላከ። የአሦርም ንጉሥ፣ የይሁዳን ንጉሥ ሕዝቅያስን ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ እንዲያገባለት ጠየቀው። ስለዚህ ሕዝቅያስ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች የሚገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው። በዚህ ጊዜም የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መዝጊያዎችና መቃኖች ላይ የለበጠውን ወርቅ ነቃቅሎ ለአሦር ንጉሥ ሰጠው። የአሦር ንጉሥ ከለኪሶ የጦሩን ጠቅላይ አዛዥ፣ ዋና አዛዡንና የጦር መሪውን ከታላቅ ሰራዊት ጋራ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ ወደ ልብስ ዐጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው የላይኛው ኵሬ ውሃ ቦይ በሚወርድበት ስፍራ ሲደርሱ ቆሙ። ወደ ንጉሡም ላኩበት፤ ከዚያም የቤተ መንግሥቱ አዛዥ፣ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ፣ ታሪክ መዝጋቢውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ሄዱ። የጦር አዛዡም እንዲህ አላቸው፤ “ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፤ “ ‘ታላቁ ንጉሥ፣ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፤ እስከዚህ የተማመንህበት ነገር ምንድን ነው? የጦር ስልትና ኀይል አለኝ ትላለህ፤ ነገር ግን ባዶ ቃል ብቻ ትናገራለህ። በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተደግፈህ ነው? እነሆ፤ እንዲህ የምትመካባት ግብጽ የሚደገፍባትን ሰው እጅ ወግታ የምታቈስል፣ የተቀጠቀጠች ሸንበቆ ናት። የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንም ለሚመኩበት ሁሉ እንደዚሁ ነው። ደግሞም፣ “በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን” የምትለኝ ከሆነ፣ የኰረብታ ላይ ማምለኪያዎቹንና መሠዊያዎቹን ሕዝቅያስ አፍርሶበት ለይሁዳና ለኢየሩሳሌም፣ “እናንተ መስገድ ያለባችሁ በዚህ መሠዊያ ፊት ብቻ ነው” ብሎ የለምን? “ ‘አሁን ናና፣ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋራ ተደራደር፤ የሚጋልቧቸው ሰዎች ካሉህ፣ ሁለት ሺሕ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። የምትመካው በግብጽ ሠረገሎችና ፈረሶች ሆኖ ሳለ፣ ከጌታዬ የበታች የጦር ሹማምት እንኳ አንዱን እንዴት መመለስ ትችላለህ? በተጨማሪም አደጋ ጥዬ ይህችን ስፍራ ለማጥቃትና ለማጥፋት የመጣሁት፣ ያለ እግዚአብሔር ይመስልሃል? በዚህች አገር ላይ ዘምቼ እንዳጠፋት የነገረኝ ራሱ እግዚአብሔር ነው።’ ” ከዚያም የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ሳምናስና ዮአስ የጦር አዛዡን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ስለምንሰማ፣ እባክህን በሶርያ ቋንቋ ተናገር፤ በቅጥሩ ላይ ያሉት ሰዎች በሚሰሙት በዕብራይስጥ አትናገረን” አሉት። ነገር ግን የጦር አዛዡ መልሶ፣ “ጌታዬ እነዚህን ቃሎች እንድናገር የላከኝ ለጌታህና ለአንተ ብቻ ነበርን? እንደ እናንተ የራሳቸውን ኵስ ለመብላትና ሽንታቸውንም ለመጠጣት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎችም አይደለምን?” አላቸው። የጦር አዛዡም ቆሞ በዕብራይስጥ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ “እንግዲህ የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ! ንጉሡ እንዲህ ይላል፤ ከእጄ ሊያድናችሁ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ ደግሞም ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር በርግጥ ያድነናል፤ ይህች ከተማ ለአሦር ንጉሥ ዐልፋ አትሰጥም’ እያለ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። “ሕዝቅያስን አትስሙ። የአሦር ንጉሥ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ከእኔ ጋራ ተስማሙ፤ ወደ እኔም ውጡ። ከዚያም እያንዳንዳችሁ ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ትበላላችሁ፤ ከጕድጓዳችሁም ውሃ ትጠጣላችሁ፤ ይኸውም የእናንተኑ ወደምትመስለው ምድር እህልና የወይን ጠጅ፣ ዳቦና የወይን ተክል፣ የወይራ ዛፍና ማር ወዳለባት እስካገባችሁ ድረስ ነው፤ እናንተም ሞትን ሳይሆን ሕይወትን ምረጡ።’ “ሕዝቅያስ፣ ‘እግዚአብሔር ይታደገናል’ በማለት ስለሚያሳስታችሁ አትስሙት። ለመሆኑ ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ የታደገ ከአሕዛብ አማልክት የትኛው ነው? የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም፣ የሄናና የዒዋም አማልክት ታዲያ የት ደረሱ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ የታደገ ማን አለ? ታዲያ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዴት ከእጄ ሊታደጋት ይችላል?” ነገር ግን ሕዝቡ ዝም አለ፤ ምንም መልስ አልሰጠም፤ ንጉሡ፣ “መልስ እንዳትሰጡ” ሲል አዝዞ ነበርና። ከዚያም የቤተ መንግሥቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሓፊው ሳምናስ እንዲሁም ታሪክ መዝጋቢው የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ የጦር አዛዡ የተናገረውንም ሁሉ ነገሩት።
2 ነገሥት 18 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ነገሥት 18
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ነገሥት 18:9-37
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች