2 ነገሥት 14:1-14

2 ነገሥት 14:1-14 NASV

የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ነገሠ። በነገሠም ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዐምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱም ዮዓዳን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ዐይነት አልነበረም፤ በማናቸውም ረገድ የአባቱን የኢዮአስን ፈለግ ተከተለ። በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር። መንግሥቱም በእጁ ከጸናለት በኋላ፣ ንጉሡን አባቱን የገደሉትን ሹማምት ገደላቸው። ይሁን እንጂ በሙሴ የሕግ መጽሐፍ እግዚአብሔር፣ “ሰው ሁሉ በገዛ ኀጢአቱ ይሙት እንጂ ወላጆች በልጆቻቸው አይገደሉ፣ ልጆችም በወላጆቻቸው ኀጢአት አይገደሉ” ሲል ያዘዘ በመሆኑ፣ የነፍሰ ገዳዩን ልጆች አልገደላቸውም። የጨው ሸለቆ በተባለው ቦታ ዐሥር ሺሕ ኤዶማውያንን ድል ያደረገ፣ ሴላን በጦርነት የያዘና እስከ ዛሬም ድረስ ዮቅትኤል ተብላ የምትጠራበትን ስም ያወጣላት አሜስያስ ነው። ከዚያም አሜስያስ የኢዩ የልጅ ልጅ፣ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ዮአስ፣ “ናና ፊት ለፊት እንጋጠም” ሲል መልእክተኞች ላከበት። የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ግን ለይሁዳ ንጉሥ ለአሜስያስ እንዲህ ሲል ላከበት፤ “አንድ የሊባኖስ ኵርንችት፣ ለአንድ የሊባኖስ ዝግባ፣ ‘ሴት ልጅህን ለልጄ ሚስት እንድትሆነው ስጠው’ አለው፤ ከዚያም አንድ የሊባኖስ ዱር አውሬ መጥቶ ኵርንችቱን በእግሩ ረገጠው። በርግጥ ኤዶምን ድል አድርገሃል፤ ልብህ በትዕቢት ተወጥሯል። ክብርህን ጠብቀህ ዐርፈህ በቤትህ ተቀመጥ! ጠብ በመጫር በራስህና በይሁዳ ላይ ውድቀት ለማምጣት ችግር የምትፈጥረው ለምንድን ነው?” አሜስያስ ግን አልሰማም፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ምድር በቤትሳሚስ ፊት ለፊት ተጋጠሙ። ይሁዳ በእስራኤል ድል ሆነ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። የእስራኤል ንጉሥ ዮአስም የአካዝያስን የልጅ ልጅ፣ የኢዮአስን ልጅ የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ቤትሳሚስ ላይ ማረከው። ከዚያም ዮአስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ ከኤፍሬም ቅጥር በር አንሥቶ የማእዘን ቅጥር በር እስከ ተባለው ድረስ ርዝመቱ አራት መቶ ክንድ ያህል ርዝመት ያለውን የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች ያለውን ወርቅ ብርና ዕቃ በሙሉ፣ በዚያም የተገኘውን ዕቃ ሁሉ በመውሰድ ምርኮኞችንም ይዞ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።