2 ቆሮንቶስ 2:1-11

2 ቆሮንቶስ 2:1-11 NASV

እንግዲህ ላሳዝናችሁ ስላልፈለግሁ ወደ እናንተ ዳግመኛ ላለመምጣት ወሰንሁ፤ እኔ ባሳዝናችሁም እንኳ፣ ከእናንተው ካሳዘንኋችሁ በቀር ደስ የሚያሠኘኝ ማን አለ? ባለፈው ጊዜ እንደዚያ የጻፍሁላችሁ ወደ እናንተ ስመጣ ደስ ሊያሠኙኝ የሚገባቸው ሰዎች እንዳያሳዝኑኝ በማለት ነው፤ ምክንያቱም የእኔ ደስታ የሁላችሁ ደስታ እንደሚሆን አምናለሁ። እንደዚያ ስጽፍላችሁ በትልቅ ሐዘንና በልብ ጭንቀት፣ በብዙም እንባ ውስጥ ነበርሁ፤ ይህንም ያደረግሁት ለእናንተ ያለኝን ጽኑ ፍቅር እንድታውቁ በማለት እንጂ እናንተን ለማሳዘን አልነበረም። ማንም ሰውን ቢያሳዝን፣ ነገር ማግነን አይሁንብኝና፣ ያሳዘነው እኔን ብቻ ሳይሆን በመጠኑም ቢሆን ሁላችሁንም ነው። እንደዚህ ያለው ሰው ብዙዎች የወሰኑበት ቅጣት በቂው ነው። ደግሞም ከልክ በላይ ዐዝኖ ተስፋ እንዳይቈርጥ፣ ይቅር ልትሉትና ልታጽናኑት ይገባችኋል። ስለዚህ አሁንም የምትወድዱት መሆናችሁን እንድትገልጹለት እለምናችኋለሁ። የጻፍሁላችሁም፣ የሚያጋጥማችሁን ፈተና መቋቋማችሁንና በሁሉም ነገር ታዛዦች መሆናችሁን ለማወቅ ነበር። እናንተ ይቅር የምትሉትን ሰው እኔም ይቅር እለዋለሁ፤ በርግጥ ይቅር የምለው ነገር ካለ፣ በክርስቶስ ፊት ይቅር የምለው ስለ እናንተ ስል ነው። ይህንም የምናደርገው ሰይጣን መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ ነው፤ የርሱን ዕቅድ አንስተውምና።