ለሰሎሞን በየዓመቱ የሚገባለት ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት የሚመዝን ወርቅ ነበር። ይህም ከታላላቅና ከተራ ነጋዴዎች ከሚገባው ቀረጥ ሌላ ነበር። መላው የዐረብ ነገሥታትና አገረ ገዦች ለሰሎሞን ወርቅና ብር ያመጡለት ነበር። ንጉሥ ሰሎሞን ሁለት መቶ ከጥፍጥፍ ወርቅ ትላልቅ ጋሻዎችን አበጀ፤ በእያንዳንዱም ጋሻ የገባው ስድስት መቶ ሰቅል ጥፍጥፍ ወርቅ ነበር። እንዲሁም ከጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ትንንሽ ጋሻዎችን አበጀ፤ በእነዚህም በእያንዳንዱ ጋሻ የገባው ጥፍጥፍ ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበር። ንጉሡም ጋሻዎቹን “የሊባኖስ ደን” በተባለው ቤተ መንግሥት ውስጥ አኖረ። ከዚያም ንጉሡ በዝኆን ጥርስ ትልቅ ዙፋን ሠርቶ በንጹሕ ወርቅ ለበጠው። ዙፋኑ ባለስድስት ደረጃ ሲሆን፣ ከዙፋኑ ጋራ የተያያዘ ከወርቅ የተሠራ የእግር መርገጫ ነበረው። መቀመጫውም ግራና ቀኙ መደገፊያ ያለው ሲሆን፣ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመዋል። በስድስቱም ደረጃዎች ጫፍ ላይ ግራና ቀኝ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመዋል። ይህን የመሰለ ዙፋን በየትኛውም አገር መንግሥት ተሠርቶ አያውቅም። ንጉሥ ሰሎሞን የሚጠጣባቸው ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ “የሊባኖስ ደን” ተብሎ በሚጠራው ቤተ መንግሥት ውስጥ የነበሩትም ዕቃዎች ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ነበሩ፤ በሰሎሞን ዘመን ብር ዋጋ እንደሌለው ስለሚቈጠር ከብር የተሠራ አንድም ነገር አልነበረም። ንጉሡ በኪራም ሰዎች የሚነዱ የተርሴስ መርከቦች ነበሩት፤ እነዚህም በየሦስት ዓመቱ አንድ ጊዜ ወርቅ፣ ብርና፣ የዝሆን ጥርስ፣ ጦጣዎችና ዝንጀሮዎች እየያዙ ይመለሱ ነበር። ንጉሥ ሰሎሞን በሀብትም ሆነ በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ ይበልጥ ነበር። የምድር ነገሥታት ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረውን ጥበብ ለመስማት ከሰሎሞን ጋራ መገናኘት ይፈልጉ ነበር። በየዓመቱም የሚመጣው ሰው ሁሉ የብርና የወርቅ ዕቃ፣ ልብስ፣ የጦር መሣሪያ፣ ቅመማ ቅመም፣ ፈረስና በቅሎ ስጦታ አድርጎ ያመጣለት ነበር። ሰሎሞን አራት ሺሕ የፈረሶችና የሠረገሎች ጋጥ ነበረው፤ እንዲሁም ንጉሡ በሚኖርበት በኢየሩሳሌምና በሠረገላ ከተሞች ዐሥራ ሁለት ሺሕ ፈረሶች ነበሩት። እርሱም ከኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብጽ ዳርቻ ድረስ ባሉት ነገሥታት ሁሉ ላይ ገዛ። ንጉሡ በኢየሩሳሌም ብሩን እንደ ማንኛውም ድንጋይ፣ የዝግባውንም ዕንጨት ብዛት በየኰረብታው ግርጌ እንደሚበቅል ሾላ አደረገው። የሰሎሞን ፈረሶች የመጡት ከግብጽና ከሌሎች አገሮች ነበር።
2 ዜና መዋዕል 9 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ዜና መዋዕል 9
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ዜና መዋዕል 9:13-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች