ከዚያም መላው የእስራኤል ጉባኤ ባለበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት እጆቹን ዘርግቶ ቆመ። ሰሎሞንም ርዝመቱ ዐምስት ክንድ፣ ወርዱ ዐምስት ክንድ፣ ከፍታውም ሦስት ክንድ የሆነ የናስ መድረክ በውጭው አደባባይ መካከል አሠርቶ ነበር፤ በመድረኩም ላይ ወጥቶ በመቆም በመላው የእስራኤል ጉባኤ ፊት ተንበርክኮ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ እንዲህም አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በፍጹም ልባቸው በመንገድህ ከሚሄዱት ባሪያዎችህ ጋራ የፍቅር ኪዳንህን የምትጠብቅ፣ በሰማይም ሆነ በምድር እንደ አንተ ያለ አምላክ የለም፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ አጽንተሃል፤ በአፍህ የተናገርኸውን ዛሬም እንደ ሆነው በእጅህ ፈጸምኸው። “አሁንም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት፣ ‘ልጆችህ አንተ እንደ አደረግኸው ሁሉ በሚያደርጉት ሁሉ ሕጌን በመጠበቅ በፊቴ ቢመላለሱ፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ በፊቴ የሚቀመጥ ሰው ፈጽሞ አታጣም’ ብለህ የሰጠኸውን ተስፋ አጽናለት። እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፣ ለባሪያህ ለዳዊት የሰጠኸው የተስፋ ቃል ይፈጸም። “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋራ በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፤ ሰማያትና ሰማየ ሰማያት እንኳ አንተን ሊይዙህ አይችሉም፤ ታዲያ እኔ የሠራሁት ይህ ቤተ መቅደስማ ምንኛ ያንስ! ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ የባሪያህን ጸሎትና ስለ ምሕረት ያቀረበውን ልመና አድምጥ፤ ባሪያህ በፊትህ የሚያቀርበውን ጩኸትና ጸሎት ስማ። ስምህ እንደሚጠራበት ወደ ተናገርኸው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ዐይኖችህ ሌትና ቀን የተከፈቱ ይሁኑ ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውንም ጸሎት ስማ። ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ በሚጸልዩበትም ጊዜ ልመናቸውን ስማ፤ ከማደሪያህ ከሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል። “አንድ ሰው ባልንጀራውን ቢበድልና እንዲምል ቢጠየቅ፣ እርሱም መጥቶ በቤተ መቅደሱ በመሠዊያህ ፊት ቢምል፣ ከሰማይ ሆነህ ስማ፤ አድርግም። በደለኛውን፣ በደሉን በራሱ ላይ አድርገህ እንደ ሥራው በመክፈል በባሪያዎችህ መካከል ፍረድ። ንጹሑም በደለኛ አለመሆኑን አስታውቅ፤ እንደ ንጽሕናውም ክፈለው። “ሕዝብህ እስራኤል አንተን ከመበደላቸው የተነሣ በጠላቶቻቸው ፊት ድል ቢሆኑ፣ ወደ አንተ ተመልሰውም በዚህ ቤተ መቅደስ ውስጥ በፊትህ በመጸለይና ልመናቸውን በማቅረብ ስምህን ቢጠሩ፣ ከሰማይ ሆነህ ስማ፤ የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለእነርሱና ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸውም ምድር መልሳቸው። “አንተን ከመበደላቸው የተነሣ፣ ሰማዩ ተዘግቶ ዝናብ ሳይዘንብ ቢቀር፣ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩና ስምህን ቢጠሩ፣ ስላስጨነቅሃቸውም ከኀጢአታቸው ቢመለሱ፣ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የባሪያዎችህን የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ የሚሄዱበትን ቀናውን መንገድ አስተምራቸው፤ ርስት አድርገህ ለሕዝብህ በሰጠሃቸውም ምድርህ ላይ ዝናብን አዝንብ። “በምድሪቱ ላይ ራብ ወይም ቸነፈር፣ ዋግ ወይም አረማሞ፣ አንበጣ ወይም ኵብኵባ በሚከሠትበት ጊዜ ወይም ከተሞቻቸውን ጠላት በሚከብብበት ጊዜ፣ እንዲሁም ማንኛውም ዐይነት ጥፋት ወይም በሽታ በሚደርስባቸው ጊዜ፣ ከሕዝብህ ማንኛውም ሰው ወይም መላው እስራኤል ጭንቀቱንና ሕመሙን ዐውቆ እጆቹን ወደዚህ ቤት በመዘርጋት ማንኛውንም ጸሎትና ልመና በሚያቀርብበት ጊዜ ሁሉ፣ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ይቅር በል፤ አድርግም። የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ የምታውቅ አንተ ብቻ ስለ ሆንህ ልቡን ለምታውቀው ለእያንዳንዱ ሰው እንደ አካሄዱ ክፈለው፤ ይኸውም እነርሱ ለአባቶቻችን በሰጠሃቸው ምድር በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ አንተን እንዲፈሩህና በመንገዶችህ እንዲሄዱ ነው። “ከሕዝብህ ከእስራኤል ወገን ያልሆነ፣ ነገር ግን ከስምህ ታላቅነት የተነሣ ከሩቅ የመጣ ባዕድ ሰው ቢኖር፣ ሰዎች ከሩቅ የሚመጡት ስለ ታላቁ ስምህ፣ ስለ ጠንካራዪቱ እጅህ፣ ስለ ተዘረጋችው ክንድህ ሰምተው ነውና፤ መጥተው ወደዚህ ቤተ መቅደስ ቢጸልዩ፣ አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የምድር ሕዝቦች ሁሉ እንደ ገዛ ሕዝብህ እንደ እስራኤል፣ ስምህን በማወቅ እንዲፈሩህ፣ የሠራሁትም ይህ ቤት ስምህ የሚጠራበት ቤት መሆኑን እንዲያውቁ ባዕዱ ሰው የሚጠይቅህን ሁሉ አድርግ። “ሕዝብህ ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ ወደምትልካቸው ቦታ ሁሉ በሚወጡበት ጊዜ፣ አንተ ወደ መረጥሃት ወደዚህች ከተማ፣ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ወደ አንተ ቢጸልዩ፣ ጸሎትና ልመናቸውን በሰማይ ሆነህ ስማ፤ ፍትሕንም አጐናጽፋቸው። “መቼም ኀጢአት የማይሠራ ሰው የለምና ሕዝብህ በአንተ ላይ ኀጢአት ቢሠሩ፣ አንተም ተቈጥተህ ለጠላቶቻቸው አሳልፈህ ብትሰጣቸው፣ እነርሱም ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ የጠላት ምድር ቢጋዙ፣ በተጋዙበት አገር ሳሉ ወደ ልቡናቸው ቢመለሱ፣ ንስሓ ቢገቡና በምርኮ ሳሉ፣ ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለናል፤ ክፉ ድርጊትም ፈጽመናል’ ብለው ቢለምኑህ፣ ተማርከው በተወሰዱበት በምርኮ ምድር ሳሉ በፍጹም ልባቸው፣ በፍጹምም ነፍሳቸው ቢመለሱና ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃቸው ምድር፣ አንተም ወደ መረጥሃት ከተማና እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤተ መቅደስ ቢጸልዩ፣ ከማደሪያህ ከሰማይ ሆነህ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን ስማ፤ ፍረድላቸውም። የበደሉህንም የሕዝብህን ኀጢአት ይቅር በል። “አሁንም አምላኬ ሆይ፤ በዚህ ስፍራ ወደ ቀረበው ጸሎት ዐይኖችህ የተገለጡ፣ ጆሮዎችህም የሚያደምጡ ይሁኑ። “አሁንም እግዚአብሔር አምላክ ሆይ ተነሥ፣ ከኀይልህ ታቦት ጋራ ወደ ማረፊያ ቦታህ ግባ። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ካህናትህ ድነትን ይልበሱ፤ ቅዱሳንህም በቸርነትህ ደስ ይበላቸው። እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ የቀባኸውን ሰው አትተወው፤ ለባሪያህ ለዳዊት ቃል የገባህለትን ጽኑ ፍቅር ዐስብ።”
2 ዜና መዋዕል 6 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ዜና መዋዕል 6
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ዜና መዋዕል 6:12-42
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች