2 ዜና መዋዕል 34:1-7

2 ዜና መዋዕል 34:1-7 NASV

ኢዮስያስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ። እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም፤ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄደ። በዘመነ መንግሥቱ በስምንተኛው ዓመት ገና ወጣት ሳለ፣ የአባቱን የዳዊትን አምላክ መፈለግ ጀመረ፤ በዐሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኰረብታ መስገጃ ስፍራዎች፣ ከአሼራ፣ ምስል ዐምዶች፣ ከተቀረጹ ጣዖታትና ቀልጠው ከተሠሩ ምስሎች አነጻ። በርሱም ትእዛዝ የበኣሊም መሠዊያዎችን አፈራረሱ፤ እርሱም ከበላያቸው የነበሩትን የዕጣን መሠዊያዎችን አደቀቀ፤ የአሼራን ምስል ዐምዶችን፣ ጣዖታቱንና ምስሎቹን ሰባብሮ ከፈጫቸው በኋላ፣ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብር ላይ በተነ። የካህናቱን ዐጥንት በመሠዊያዎቻቸው ላይ አቃጠለ፤ በዚህ ዐይነትም ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አነጻ። እስከ ንፍታሌም ባሉ በምናሴ፣ በኤፍሬምና በስምዖን ከተሞች እንዲሁም በዙሪያቸው ባሉ የፈራረሱ አካባቢዎች፣ መሠዊያዎችንና የአሼራ ምስል ዐምዶችን አፈራረሰ፤ ጣዖታቱን እንደ ዱቄት አደቀቀ፤ በመላው እስራኤል የሚገኙትንም የዕጣን መሠዊያዎች አነካከተ፤ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።