ዖዝያን ከበረታ በኋላ ግን ዕብሪቱ ለውድቀት ዳረገው። በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመግባቱ አምላኩን እግዚአብሔርን በደለ፤ ካህኑም ዓዛርያስ ቈራጥ ከሆኑ ከሌሎች ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ጋራ ተከትሎት ገባ። እነርሱም ፊት ለፊት በመጋፈጥ፣ “ዖዝያን ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ማጠን ለተለዩትና የአሮን ዘሮች ለሆኑት ለካህናቱ እንጂ ለአንተ የተገባ አይደለም፤ እግዚአብሔርን አልታመንህምና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድም ክብር አይሆንልህምና” አሉት። ጥና በእጁ ይዞ ዕጣን ለማጠን ዝግጁ የነበረው ዖዝያን ተቈጣ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ በዕጣን መሠዊያው ፊት ሆኖ ካህናቱ ላይ እየተቈጣ ሳለ፣ በግንባሩ ላይ የቈዳ በሽታ ወጣበት። ሊቀ ካህናቱ ዓዛርያስና ሌሎቹ ካህናት ሁሉ በተመለከቱት ጊዜ፣ በግንባሩ ላይ ለምጽ እንደ ወጣበት አዩ። ስለዚህ አጣድፈው አስወጡት፤ በርግጥ እርሱም ራሱ ለመውጣት ቸኵሎ ነበር፤ እግዚአብሔር አስጨንቆታልና። ንጉሥ ዖዝያን እስከሚሞትበትም ቀን ድረስ ለምጽ ነበረበት። ለምጻም በመሆኑም ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተወግዶ ነበርና በተለየ ቤት ተቀመጠ። በዚያ ጊዜ ቤተ መንግሥቱን በኀላፊነት የሚመራውና የአገሩንም ሕዝብ የሚያስተዳድረው የንጉሡ ልጅ ኢዮአታም ነበር። በዖዝያን ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የተከናወነውን ሌላውን ተግባር ሁሉ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ጽፎታል። ዖዝያንም ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ። ሕዝቡም “ለምጽ አለበት” ብለው የነገሥታቱ በሆነው መቃብር አጠገብ ባለው ቦታ ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በምትኩ ነገሠ።
2 ዜና መዋዕል 26 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ዜና መዋዕል 26
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ዜና መዋዕል 26:16-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች