2 ዜና መዋዕል 24:17-27

2 ዜና መዋዕል 24:17-27 NASV

ከዮዳሄ ሞት በኋላ የይሁዳ ሹማምት መጥተው ለንጉሡ ታማኝነታቸውን ገለጹ፤ ንጉሡም አደመጣቸው። እነርሱም የአባቶቻቸውን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ትተው፣ የአሼራን ዐምዶችና ጣዖታትን አመለኩ፤ በበደላቸውም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ መጣ። ወደ እግዚአብሔር ይመልሷቸው ዘንድ እርሱ ነቢያቱን ወደ ሕዝቡ ሰደደ፤ ነቢያቱም መሰከሩባቸው፤ እነርሱ ግን አላዳመጡም። የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆሞ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይሳካላችሁም፤ እናንተ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁት እርሱም ትቷችኋል’ ” አላቸው። እነርሱ ግን አሤሩበት፤ በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ ላይ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሥ ኢዮአስ የዘካርያስ አባት ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፤ በዚህ ፈንታ ልጁን ገደለው፤ በሚሞትበትም ጊዜ፣ “እግዚአብሔር ይየው፤ እርሱው ይበቀልህ” አለ። በዓመቱም መጨረሻ፣ የሶርያ ሰራዊት በኢዮአስ ላይ ዘመተ፤ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምንም ወርሮ የሕዝቡን መሪዎች ሁሉ ደመሰሰ፤ ምርኮውንም ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ደማስቆ ላከ። የሶርያ ሰራዊት ሰዎች ጥቂት ቢሆኑም እንኳ እግዚአብሔር በጣም የሚበልጠውን ሰራዊት በእጃቸው አሳልፎ ሰጠ፤ ይሁዳ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ በኢዮአስ ላይ ተፈረደበት። ሶርያውያንም በወጡ ጊዜ ኢዮአስን ክፉኛ አቍስለው፣ ጥለውት ሄዱ፤ የካህኑን የዮዳሄን ልጅ ስለ ገደለም፣ ሹማምቱ አሢረውበት በዐልጋው ላይ እንዳለ ገደሉት። በዚህ ሁኔታም ሞቶ በዳዊት ከተማ ተቀበረ እንጂ በነገሥታቱ መቃብር አልተቀበረም። በርሱ ላይ ያሤሩትም የአሞናዊቱ የሰምዓት ልጅ ዛባድና የሞዓባዊቱ የሰማሪት ልጅ ዮዛባት ነበሩ። የወንዶች ልጆቹ ታሪክ፣ ስለ እርሱ የተነገሩት ብዙ ትንቢቶችና የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መታደስ በነገሥታቱ የታሪክ መዛግብት ተጽፈዋል። ልጁ አሜስያስም በርሱ ፈንታ ነገሠ።