2 ዜና መዋዕል 21:4-17

2 ዜና መዋዕል 21:4-17 NASV

ኢዮራም በአባቱ መንግሥት ላይ ተደላድሎ ከተቀመጠ በኋላ፣ ወንድሞቹን በሙሉ ከጥቂት የእስራኤል አለቆች ጋራ በሰይፍ ገደለ። ኢዮራም በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሠላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ። እርሱም የአክዓብን ልጅ አግብቶ ስለ ነበር፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም የእስራኤል ነገሥታት የሄዱበትን መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከዳዊት ጋራ ካደረገው ኪዳን የተነሣ፣ የዳዊትን ቤት ማጥፋት አልፈለገም፤ ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም መብራት እንደሚሰጥ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና። በይሆራም ዘመነ መንግሥት ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐምፆ፣ የራሱን ንጉሥ አነገሠ። ስለዚህ ኢዮራም የጦር ሹማምቱና ሠረገላዎቹን ሁሉ አሰልፎ ተሻገረ። በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሠረገላ አዛዦቹን ሁሉ የከበቧቸውን ኤዶማውያንን መታ። ኤዶም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንዳመፀ ነው፤ ልብናም በዚሁ ጊዜ ዐመፀ። ይሆራም የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ትቶ ነበርና። ከዚህም በላይ በይሁዳ ኰረብቶች ላይ መስገጃ ስፍራዎች ሠርቶ የኢየሩሳሌም ሕዝብ በዚያ እንዲያመነዝር አደረገ፤ ይሁዳንም አሳተ። ከነቢዩ ከኤልያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለኢዮራም መጣ፤ “የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አንተ በአባትህ በኢዮሣፍጥ ወይም በይሁዳ ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህም፤ ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደሃል፤ የአክዓብ ቤት የእስራኤልን ሕዝብ እንዲያመነዝር እንዳደረገ ሁሉ፣ አንተም ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ እንዲያመነዝሩ አሳሳትሃቸው፤ እንዲሁም ካንተ የሚሻሉትን፣ የገዛ ወንድሞችህንና የአባትህን ቤተ ሰብ አባላት ገደልሃቸው፤ ስለዚህ እነሆ፤ እግዚአብሔር ሕዝብህን፣ ልጆችህን፣ ሚስቶችህንና ያለህን ሁሉ በታላቅ መቅሠፍት ይመታል። አንተም ራስህ በየዕለቱ እየባሰ በሚሄድ የአንጀት በሽታ ክፉኛ ትታመማለህ፤ በመጨረሻም ሕመሙ አንጀትህን ወደ ውጭ ያወጣዋል።’ ” እግዚአብሔርም ፍልስጥኤማውያንንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩ ዐረቦችን በኢዮራም ላይ በጠላትነት እንዲነሡ አደረገ። እነርሱም በይሁዳ ላይ ወጡ፤ ወረሯትም። በንጉሡ ቤተ መንግሥት የሚገኘውን ዕቃ ሁሉ፣ ከወንዶች ልጆቹና ከሚስቶቹ ጋራ ወሰዱ፤ ከመጨረሻ ልጁ ከአካዝያስ በቀር አንድም ልጅ አልቀረለትም።