2 ዜና መዋዕል 15:1-19

2 ዜና መዋዕል 15:1-19 NASV

የእግዚአብሔር መንፈስ በዖዴድ ልጅ በአዛርያስ ላይ መጣ። እርሱም አሳን ሊገናኘው ወጣ፤ እንዲህም አለው፤ “አሳ፣ እናንተም ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፤ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋራ ስትሆኑ፣ እርሱም ከእናንተ ጋራ ይሆናል፤ ብትፈልጉት ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን፣ ይተዋችኋል። እስራኤል ያለ እውነተኛ አምላክ፣ ያለ አስተማሪ ካህንና ያለ ሕግ ብዙ ዘመን አሳልፈዋል። በመከራቸው ጊዜ ግን፣ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ፈለጉት፤ እርሱም ተገኘላቸው። በዚያ ዘመን በምድር ነዋሪዎች ሁሉ ዘንድ ታላቅ ሁከት ስለ ነበር፣ በሰላም ወጥቶ መግባት አስተማማኝ አልነበረም። እግዚአብሔር በተለያየ መከራ ያስጨንቃቸው ስለ ነበር፣ አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት፣ አንዱም ከተማ በሌላው ከተማ ይደመሰስ ነበር። እናንተ ግን የድካማችሁን ዋጋ ስለምታገኙ በርቱ፤ እጃችሁም አይላላ።” አሳ ይህን ቃልና የነቢዩን የዖዴድን ልጅ የዓዛርያስን ትንቢት በሰማ ጊዜ በረታ። ከመላው ይሁዳና ከብንያም ምድር፣ በኤፍሬምም ኰረብቶች ላይ ከያዛቸው ከተሞች አስጸያፊዎቹን ጣዖታት አስወገደ። ከእግዚአብሔር መቅደስ ሰበሰብ ፊት ለፊት የነበረውንም የእግዚአብሔር መሠዊያ ዐደሰ። አምላኩ እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ መሆኑን ባዩ ጊዜ፣ ከእስራኤል ብዙ ሰዎች እርሱን ተጠግተው ነበር፤ እርሱም ይሁዳንና ብንያምን እንዲሁም ከኤፍሬም፣ ከምናሴና ከስምዖን መጥተው ከእነርሱ ጋራ የተቀመጡትን ሰበሰበ። እነርሱም በአሳ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ ዐምስተኛው ዓመት፣ በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። በዚያ ጊዜ በምርኮ ካመጡት ውስጥ ሰባት መቶ በሬ፣ ሰባት ሺሕ በግና ፍየል ለእግዚአብሔር ሠዉ። የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ይሹ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረጉ። የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የማይፈልግ ሁሉ ግን፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ፣ ወንድም ሆነ ሴት እንዲገደል አደረጉ። ይህንም በታላቅ ድምፅ፣ በእልልታ፣ በእንቢልታና በመለከት ድምፅ ለእግዚአብሔር ማሉ። በፍጹም ልባቸው ስለ ማሉም የይሁዳ ሕዝብ በመሐላው ደስ ተሠኙ። እግዚአብሔርን ከልብ ፈለጉት፤ እርሱም ተገኘላቸው፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በሁሉም አቅጣጫ ዕረፍት ሰጣቸው። እንዲሁም ንጉሡ አሳ ለአስጸያፊዋ የአሼራ ጣዖት ዐምድ በማቆሟ፣ አያቱን መዓካን ከእቴጌነቷ ሻራት፤ ጣዖቷንም ሰባብሮ በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው። አሳ የማምለኪያ ኰረብቶችን ከእስራኤል ፈጽሞ ባያስወግድም እንኳ፣ በዘመኑ ሁሉ ልቡ ፍጹም ነበር። እርሱና አባቱ የቀደሱትን ብር፣ ወርቅና ልዩ ልዩ ዕቃዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አስገባ። እስከ ሠላሳ ዐምስተኛው የአሳ ዘመነ መንግሥት ድረስ ምንም ዐይነት ጦርነት አልነበረም።