2 ዜና መዋዕል 11:5-23

2 ዜና መዋዕል 11:5-23 NASV

ሮብዓም መኖሪያውን በኢየሩሳሌም በማድረግ ለመከላከያ የሚሆኑ ከተሞችን በይሁዳ ሠራ፤ እነዚህም ቤተ ልሔም፣ ኤጣም፣ ቴቁሔ፣ ቤትጹር፣ ሦኮን፣ ዓዶላም፣ ጋት፣ መሪሳ፣ ዚፍ፣ አዶራይም፣ ለኪሶ፣ ዓዜቃ፣ ጾርዓ፣ ኤሎን፣ ኬብሮን ናቸው። በይሁዳና በብንያም ውስጥ የተመሸጉት ከተሞች እነዚህ ነበሩ። እነዚህንም ምሽጎቻቸውን አጠንክሮ፣ አዛዦችን ሾመባቸው፤ ምግብ፣ ዘይትና የወይን ጠጅ አከማቸባቸው። በየከተሞቹም ሁሉ ጋሻና ጦር አከማችቶ ይበልጥ አጠናከራቸው። በዚህ ዐይነት ይሁዳንና ብንያምን የራሱ አደረገ። በመላው እስራኤል ያሉት ካህናትና ሌዋውያን ከየክልላቸው ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። ኢዮርብዓምና ልጆቹ ሌዋውያኑን ከእግዚአብሔር የክህነት አገልግሎት ስላባረሯቸው ሌዋውያኑ ማሰማሪያ ቦታቸውንና ንብረታቸውን ሁሉ ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ እርሱም ለየኰረብታው መስገጃ እንዲሁም ለሠራቸው የፍየልና የጥጃ ምስሎች የራሱን ካህናት ሾመ። ከእያንዳንዱም የእስራኤል ነገድ ከልባቸው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሁሉ፣ ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፣ ሌዋውያኑን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ። በዚሁ ሁኔታ የዳዊትንና የሰሎሞንን መንገድ በመከተል፣ ለሦስት ዓመት የይሁዳን መንግሥት አበረቱ፤ የሰሎሞንን ልጅ ሮብዓምንም ረዱ። ሮብዓም መሐላትን አገባ፤ አባቷ የዳዊት ልጅ ኢያሪሙት ሲሆን፣ እናቷም አቢካኢል የተባለች፣ የእሴይ የልጅ ልጅ የኤልያብ ልጅ ነበረች። እርሷም የዑስ፣ ሰማርያና ዛሃም የተባሉ ወንዶች ልጆች ወለደችለት። ከዚያም የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን አገባ፤ እርሷም አብያ፣ ዓታይ፣ ዚዛ፣ ሰሎሚት የተባሉትን ወለደችለት። ሮብዓም መዓካን የአቤሴሎምን ሴት ልጅ ከሌሎቹ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ይልቅ አብልጦ ወደዳት። በአጠቃላይ ዐሥራ ስምንት ሚስትና ስድሳ ቁባት፣ ሃያ ስምንት ወንድና ስድሳ ሴት ልጆች ነበሩት። ሮብዓም የመዓካን ልጅ አብያን ሊያነግሠው ስለ ፈለገ ከልዑላን ወንድሞቹ አልቆ ዋና አደረገው። ከወንዶች ልጆቹም ጥቂቱን በይሁዳና በብንያም አውራጃዎች እንዲሁም በተመሸጉት ከተሞች ስለ ሾማቸው፣ ዘዴኛነቱን አሳይቷል። የሚያስፈልጋቸውን በብዛት ሰጣቸው፤ ብዙ ሚስቶችም አጋባቸው።