1 ጢሞቴዎስ 3
3
እረኞችና ዲያቆናት
1“ማንም ኤጲስቆጶስነትን#3፥1 ወይም ተመልካች፣ ጠባቂዎች ቢፈልግ፣ መልካም ሥራን ይመኛል” የሚለው ቃል የታመነ ነው። 2እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ኤጲስ ቆጶስ የማይነቀፍ፣ የአንዲት ሚስት ባል፣ ልከኛ፣ ራሱን የሚገዛ፣ በሥርዐት የሚኖር፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ማስተማር የሚችል፣ 3የማይሰክር፣ የማይጣላ ግን ጨዋ የሆነ፣ የማይጨቃጨቅ፣ ገንዘብንም የማይወድ ሊሆን ይገባዋል። 4ልጆቹን ታዛዥና አክባሪ አድርጎ በማሳደግ የገዛ ቤተ ሰቡን በአግባቡ የሚያስተዳድር ሊሆን ይገባል። 5አንድ ሰው የራሱን ቤት ማስተዳደር ካላወቀበት፣ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ሊጠብቅ ይችላል? 6በትዕቢት ተነፍቶ ዲያብሎስ በወደቀበት ፍርድ እንዳይወድቅ አዲስ ክርስቲያን አይሁን። 7ደግሞም ስሙ እንዳይነቀፍና በዲያብሎስ ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቅ፣ በውጭ ባሉት ዘንድ መልካም ምስክርነት ሊኖረው ይገባል።
8ዲያቆናትም#3፥8 ዲያቆናት የሚለው ቃል የሚያመለክተው ክርስቲያኖች ሆነው የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ወይም ሽማግሌዎችን በተለያየ መልኩ የሚረዱ አገልጋዮችን ነው። በተመሳሳይ መልኩ ቍ 12፤ ሮሜ 16፥1 እና በፊል 1፥1 ላይ እናገኘዋለን። እንደዚሁ የተከበሩ፣ ቃላቸውን የማይለዋውጡ፣ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጐመጁ፣ ያለ አግባብ የሚገኝ ጥቅምንም የማያሳድዱ ሰዎች መሆን ይገባቸዋል፤ 9የእምነትንም ጥልቅ ምስጢር በንጹሕ ኅሊና መጠበቅ አለባቸው። 10እነርሱም አስቀድመው ይፈተኑ፤ ከዚያም፣ አንዳች ነቀፋ ካልተገኘባቸው በዲቁና ያገልግሉ።
11እንዲሁ ሴቶችም#3፥11 የዲያቆናት ሚስቶችን ወይም ሴት ዲያቆናትን ያመለክታል። የተከበሩ፣ ሐሜተኞች ያልሆኑ ነገር ግን ልከኞችና በነገር ሁሉ የታመኑ ሊሆኑ ይገባል።
12ዲያቆናት የአንዲት ሚስት ባል መሆን ይገባቸዋል፤ ደግሞም ልጆቻቸውንና ቤተ ሰቦቻቸውን በአግባቡ የሚያስተዳድሩ መሆን አለባቸው። 13በአግባቡ ያገለገሉ ለራሳቸው ትልቅ ክብርን፣ በክርስቶስ ኢየሱስም ባላቸው እምነት ብዙ ድፍረትን ያገኛሉ።
ጳውሎስ መመሪያዎች የሰጠባቸው ምክንያቶች
14ወደ አንተ ቶሎ ለመምጣት ተስፋ ባደርግም ይህን ትእዛዝ እጽፍልሃለሁ፤ 15ይህንም የምጽፍልህ ብዘገይ እንኳ ሰዎች በእግዚአብሔር ቤት እንዴት መኖር እንዳለባቸው እንድታውቅ ነው፤ ቤቱም የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፣ ይኸውም የእውነት ዐምድና መሠረት ነው። 16የእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ምስጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤
እርሱ በሥጋ ተገለጠ፤
በመንፈስ#3፥16 ወይም በመንፈስም ጸደቀ፤
በመላእክት ታየ፤
በአሕዛብ ዘንድ ተሰበከ፤
በዓለም ባሉት ታመነ፤
በክብር ዐረገ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.