1 ሳሙኤል 28:15-25

1 ሳሙኤል 28:15-25 NASV

ሳሙኤልም ሳኦልን፣ “አስነሥተህ የምታውከኝ ለምንድን ነው?” አለው። ሳኦልም፣ “እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ፍልስጥኤማውያን እየወጉኝ ነው፤ እግዚአብሔርም ከእኔ ርቋል፤ በነቢያትም ሆነ በሕልም አልመለሰልኝም፤ ስለዚህ ምን ማድረግ እንደሚገባኝ እንድትነግረኝ ጠራሁህ” አለው። ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “ታዲያ እግዚአብሔር ከራቀህ፣ ጠላትም ከሆነህ ለምን ትጠይቀኛለህ? እግዚአብሔር በእኔ የተናገረውን አድርጓል፤ እግዚአብሔር መንግሥትህን ከእጅህ ነጥቆ ለጎረቤትህ ለዳዊት ሰጥቶታል። ለእግዚአብሔር ስላልታዘዝህ፣ ታላቅ ቍጣውንም በአማሌቃውያን ላይ ስላልፈጸምህ እግዚአብሔር ዛሬ ይህን አድርጎብሃል። እግዚአብሔር አንተንና እስራኤልን ለፍልስጥኤማውያን አሳልፎ ይሰጣል፤ አንተና ልጆችህም ነገ ከእኔ ጋራ ትሆናላችሁ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር የእስራኤልን ሰራዊት ለፍልስጥኤማውያን አሳልፎ ይሰጣል።” ሳሙኤል ከተናገረው ቃል የተነሣ፣ ሳኦል በፍርሀት ተውጦ ወዲያውኑ በቁመቱ ሙሉ መሬት ላይ ወደቀ፤ ቀኑንና ሌሊቱን ሁሉ እህል ስላልቀመሰ ጕልበቱ ዝሎ ነበር። ሴትዮዋ ወደ ሳኦል መጥታ እጅግ መደንገጡን ባየች ጊዜ እንዲህ አለችው፤ “እነሆ፤ አገልጋይህ ቃልህን ሰምቻለሁ፤ በነፍሴም ቈርጬ የነገርኸኝን ፈጽሜአለሁ። አሁንም እባክህ አገልጋይህ የምትልህን ስማ፤ ብርታት አግኝተህ መሄድ እንድትችል፣ ጥቂት ምግብ ላቅርብልህና ብላ።” እርሱም፣ “አልበላም” በማለት እንቢ አለ። ነገር ግን የራሱ ሰዎች ከሴትየዋ ጋራ ሆነው አጥበቀው ስለ ለመኑት ቃላቸውን ሰማ፤ ከመሬትም ተነሥቶ በዐልጋ ላይ ተቀመጠ። ሴትዮዋም በቤቷ የሠባ ጥጃ ስለ ነበራት፣ ፈጥና ዐረደችው፤ ዱቄት ወስዳ ለወሰች፣ ቂጣም ጋገረች። ከዚያም ለሳኦልና ለሰዎቹ አቀረበችላቸው፤ እነርሱም በሉ፤ በዚያም ሌሊት ተነሥተው ሄዱ።