ሳሙኤልም ሞተ፤ እስራኤል ሁሉ ተሰብስበው አለቀሱለት፤ አርማቴም ባለው ቤቱም ቀበሩት። ከዚያም ዳዊት ተነሥቶ ወደ ፋራን ምድረ በዳ ወረደ። በማዖን ምድር በቀርሜሎስ ንብረት ያለው አንድ ባለጠጋ ሰው ነበረ፤ እርሱም አንድ ሺሕ ፍየሎችና በቀርሜሎስ የሚሸልታቸው ሦስት ሺሕ በጎች ነበሩት። የሰውየው ስም ናባል፣ የሚስቱም ስም አቢግያ ነበረ። እርሷም አስተዋይና ውብ ነበረች፤ ባሏ ግን ባለጌና ምግባረ ብልሹ ሰው ነበረ፤ እርሱም ከካሌብ ወገን ነበር። ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ናባል በጎቹን እንደሚሸልት ሰማ። እርሱም ዐሥር ወጣቶችን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ቀርሜሎስ ወደ ናባል ውጡ፤ በስሜም ሰላምታ አቅርቡለት። እንዲህም በሉት፤ ‘ዕድሜህ ይርዘም! ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ሰላም ለቤተ ሰብህና የአንተ ለሆነው ሁሉ ይሁን። “ ‘በዚህ ጊዜ በጎች እንደምትሸልት ሰምቻለሁ፤ እረኞችህ ከእኛ ጋራ በነበሩበት ጊዜ፣ ያደረስንባቸው ጕዳት የለም፤ ቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ፣ የጠፋባቸው አንዳች ነገር አልነበረም። የገዛ አገልጋዮችህን ጠይቅ፤ እነርሱም ይነግሩሃል። ስለዚህ አመጣጣችን በጥሩ ቀን በመሆኑ፣ እነዚህ ወጣቶቼ በፊትህ ሞገስ ያግኙ። እባክህን ለአገልጋዮችህና ለልጅህ ለዳዊት የምትችለውን ያህል ስጥ።’ ” የዳዊት ሰዎች ከዚያ እንደ ደረሱም፣ በዳዊት ስም ይህንኑ መልእክት ለናባል ከተናገሩ በኋላ ምላሹን ይጠባበቁ ጀመር። ናባልም ለዳዊት አገልጋዮች እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ለመሆኑ ይህ ዳዊት ማነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? በአሁኑ ጊዜ ከጌቶቻቸው የሚኰበልሉ አገልጋዮች ብዙ ናቸው። ታዲያ እንጀራዬንና ውሃዬን እንዲሁም በጎቼን ለሚሸልቱልኝ ሰዎች ያረድሁትን ፍሪዳ ከየት እንደ መጡ ለማይታወቁ ሰዎች የምሰጠውስ ለምንድን ነው?” የዳዊት ሰዎችም ወደ መጡበት ተመለሱ፤ እዚያም እንደ ደረሱ የተባሉትን ሁሉ ነገሩት። ዳዊትም ሰዎቹን፣ “በሉ ሁላችሁም ሰይፋችሁን ታጠቁ” አላቸው። ስለዚህ ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፤ ዳዊትም የራሱን ታጠቀ። አራት መቶ ያህል ሰዎች ከዳዊት ጋራ ሲወጡ መቶ ያህሉ ግን ጓዝ ለመጠበቅ ቀሩ። ከአገልጋዮቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢግያ እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ ዳዊት ሰላምታውን እንዲያቀርቡለት ከምድረ በዳ ወደ ጌታችን መልእክተኞችን ልኮ ነበር፤ እርሱ ግን የስድብ ናዳ አወረደባቸው። እነዚህ ሰዎች ግን እጅግ መልካም ነበሩ፤ ጕዳትም አላደረሱብንም፤ በዱር ዐብረናቸው በነበርንበት ጊዜም ሁሉ፣ ምንም ነገር አልጠፋብንም። በጎቻችንን እየጠበቅን ዐብረናቸው ባሳለፍነው ጊዜ ሁሉ፣ ቀንም ሆነ ሌሊት በዙሪያችን ዐጥር ሆነውን ነበር። አሁንም በጌታችንና በመላው ቤተ ሰቡ ላይ መከራ እያንዣበበ ስለ ሆነ፣ አስቢበትና የምታደርጊውን አድርጊ፤ እርሱ እንደ ሆነ እንዲህ ያለ ምናምንቴ ሰው ስለ ሆነ፣ ደፍሮ የሚነግረው አንድም ሰው የለም።” አቢግያም ጊዜ አላጠፋችም፤ ሁለት መቶ እንጀራ፣ ሁለት አቍማዳ የወይን ጠጅ፣ ዐምስት የተሰናዱ በጎች፣ ዐምስት መስፈሪያ የተጠበሰጠ እሸት፣ መቶ የወይን ዘለላና ዘቢብ፣ ሁለት መቶ ጥፍጥፍ የበለስ ፍሬ ወስዳ በአህዮች ላይ ጫነች። ከዚያም አገልጋዮቿን፣ “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋለሁ” አለቻቸው፤ ለባሏ ለናባል ግን አልነገረችውም። እርሷም በአህያዋ ላይ ተቀምጣ ወደ ሸለቆው በምትወርድበት ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርሷ ወረዱ፤ እርሷም አገኘቻቸው። ዳዊትም እንዲህ ብሎ ነበር፤ “ምንም ነገር እንዳይጠፋበት የዚህን ሰው ሀብት በምድረ በዳ ያን ያህል መጠበቄ ለካ በከንቱ ኖሯል፤ ደግ በሠራሁ ይኸው ክፉ መለሰልኝ። ነገ ጧት የርሱ ከሆነው ሁሉ አንድ ወንድ እንኳ በሕይወት ባስቀር እግዚአብሔር በዳዊት ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ያድርግበት፣ ከዚህም የከፋ ይጨምርበት!” አቢግያም ዳዊትን ባየች ጊዜ ወዲያው ከአህያዋ ወርዳ፣ በዳዊትም ፊት በግምባሯ ተደፍታ እጅ ነሣች። በእግሩም ላይ ወድቃ እንዲህ አለች፤ “ጌታዬ ሆይ፤ በደሉ በእኔ ላይ ብቻ ይሁን፤ እባክህ አገልጋይህ ታናግርህ፤ የምትልህንም ስማ። ጌታዬ፣ ያን ምናምንቴ ሰው ናባልን ከቁም ነገር አይቍጠረው፤ ስሙ ራሱ ሞኝ ማለት ስለ ሆነ፣ ሰውየውም ልክ እንደ ስሙ ነው፤ ሞኝነትም ዐብሮት የኖረ ነው። እኔ አገልጋይህ ግን ጌታዬ የላካቸውን ጕልማሶች አላየኋቸውም። ጌታዬ ሆይ፤ ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ደም ከማፍሰስና በገዛ እጅህ ከመበቀል የጠበቀህ እግዚአብሔር ነው፤ አሁንም ጠላቶችህና ጌታዬን ሊጐዱ የሚፈልጉ ሁሉ እንደ ናባል ይሁኑ፤ አገልጋይህም ለጌታዬ ያመጣችው ይህ ስጦታ አንተን ለሚከተሉ ጕልማሶች ይሰጥ። “ጌታዬ የእግዚአብሔርን ጦርነት ስለሚዋጋ እግዚአብሔርም ለጌታዬ ሥርወ መንግሥቱን በርግጥ ለዘላለም የሚያጸናለት በመሆኑ፣ እባክህ የእኔን የአገልጋይህን በደል ይቅር በል፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ ክፋት አይገኝብህ። ማንም ሰው ሕይወትህን ለማጥፋት ቢያሳድድህ እንኳ፣ የጌታዬ ሕይወት በሕያዋን አንድነት እስራት ውስጥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ በሰላም ትጠበቃለች፤ የጠላቶችህን ሕይወት ግን፣ እንደ ወንጭፍ ድንጋይ ይወነጭፋል። እግዚአብሔር ለጌታዬ በሰጠው ተስፋ መሠረት በጎውን ነገር ሁሉ ባደረገለትና በእስራኤልም ላይ ባነገሠው ጊዜ፣ ጌታዬ የምታዝንበት ምክንያት ወይም የኅሊና ጸጸት አይኖርህም፤ በከንቱ ያፈሰስኸውም ደም ሆነ በገዛ እጅህ የተበቀልኸው የለምና። እግዚአብሔር በጎ ነገር ባደረገልህ ጊዜ እኔን አገልጋይህን ዐስበኝ።” ዳዊትም አቢግያን እንዲህ አላት፤ “ዛሬ እንድታገኚኝ ወደ እኔ የላከሽ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። ደም እንዳላፈስስና በገዛ እጄ እንዳልበቀል ዛሬ ስለ ጠበቅሽኝ ስለ በጎ ሐሳብሽ አንቺም የተባረክሽ ሁኚ። ጕዳት እንዳላደርስብሽ የጠበቀኝ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! እንዲህ በቶሎ መጥተሽ ባታገኚኝ ኖሮ፣ እስኪነጋ ድረስ ለናባል አንድ ወንድ እንኳ ባልተረፈ ነበር።” ከዚያም ዳዊት ያመጣችለትን ከእጇ ተቀብሎ፣ “በሰላም ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፤ ቃልሽን ሰምቻለሁ፤ የጠየቅሽኝንም ተቀብያአለሁ” አላት።
1 ሳሙኤል 25 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ሳሙኤል 25
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ሳሙኤል 25:1-35
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች