1 ሳሙኤል 17:45-49

1 ሳሙኤል 17:45-49 NASV

ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን እንዲህ አለው፤ “አንተ ሰይፍ፣ ጦርና ጭሬ ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን አንተ በተገዳደርኸው የእስራኤል ሰራዊት ጌታ በሆነው፣ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እኔ መትቼ እጥልሃለሁ፤ ራስህንም እቈርጠዋለሁ። በዚህች ዕለት የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ሬሣ ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ፣ ዓለምም ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አምላክ መኖሩን ያውቃል። እዚህ የተሰበሰቡትም ሁሉ፣ እግዚአብሔር የሚያድነው በሰይፍ ወይም በጦር እንዳልሆነ ያውቃሉ፤ ሰልፉ የእግዚአብሔር ስለ ሆነም ሁላችሁን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።” ፍልስጥኤማዊው ሊመታው በቀረበ ጊዜ፣ ዳዊትም ሊገጥመው ወደ ውጊያው ሜዳ በፍጥነት ሮጠ። እጁንም ወደ ኰረጆው በመስደድ አንድ ድንጋይ አውጥቶ ወነጨፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩ ላይ መታው። ድንጋዩም ግንባሩ ውስጥ ገብቶ ተቀረቀረ፤ ፍልስጥኤማዊውም በግምባሩ ተደፋ።