1 ሳሙኤል 13:5-10

1 ሳሙኤል 13:5-10 NASV

ፍልስጥኤማውያን ሦስት ሺሕ ሠረገሎች፣ ስድስት ሺሕ ፈረሰኞች ቍጥሩ እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ሰራዊት ይዘው እስራኤልን ለመውጋት ተሰበሰቡ፤ ወጥተውም ከቤትአዌን በስተምሥራቅ ባለችው በማክማስ ሰፈሩ። እስራኤላውያን፣ ያሉበት ሁኔታ እጅግ የሚያሠጋ መሆኑንና ሰራዊታቸውም በከባድ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ባዩ ጊዜ፣ በየዋሻውና በየእሾኽ ቍጥቋጦው፣ በየዐለቱ መካከልና በየገደሉ እንዲሁም በየጕድጓዱ ሁሉ ተደበቁ። ከዕብራውያንም አንዳንዶቹ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ። ሳኦል ግን በጌልገላ ቈየ፣ ዐብሮት የነበረውም ሰራዊት ሁሉ በፍርሀት ይንቀጠቀጥ ነበር። እርሱም ሳሙኤል በሰጠው ቀጠሮ መሠረት ሰባት ቀን ጠበቀው። ነገር ግን ሳሙኤል ወደ ጌልገላ አልመጣም፤ የሳኦልም ሰራዊት መበታተን ጀመረ። በዚህ ጊዜ ሳኦል፣ “የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን አምጡልኝ” አለ። ከዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ። ልክ መሥዋዕቱን አቅርቦ እንዳበቃ፣ ወዲያውኑ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም እንዲመርቀው ሊቀበለው ወጣ።