1 ሳሙኤል 11:1-15

1 ሳሙኤል 11:1-15 NASV

አሞናዊው ናዖስ ወጥቶ ኢያቢስ ገለዓድን ከበባት፤ የኢያቢስም ሰዎች ሁሉ፣ “ከእኛ ጋራ ቃል ኪዳን አድርግ፣ እኛም እንገዛልሃለን” አሉት። አሞናዊው ናዖስ፣ “ከእናንተ ጋራ ቃል ኪዳን የማደርገው የእያንዳንዳችሁን ቀኝ ዐይን አውጥቼ እስራኤልን ሁሉ ካዋረድሁ በኋላ ብቻ ነው” ሲል መለሰ። የኢያቢስም ሽማግሌዎች፣ “ወደ መላው እስራኤል መልእክተኞችን እንድንልክ የሰባት ቀን ጊዜ ስጠን፤ ሊታደገን የሚመጣ ሰው ከሌለ፣ ለአንተ እንገዛለን” አሉት። መልእክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው ይህን ለሕዝቡ በተናገሩ ጊዜ፣ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ በዚህ ጊዜ፣ ሳኦል በሬዎቹን እየነዳ ከዕርሻ ተመለሰ፤ እርሱም፣ “ሕዝቡ የሚያለቅሰው ምን ሆኖ ነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም የኢያቢስ ሰዎች ያሏቸውን ነገሩት። ሳኦል ይህን በሰማ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ እጅግ ተቈጣ። ጥንድ በሬዎች ወስዶ ቈራረጠ፤ ሥጋቸውንም በመልእክተኞች እጅ ልኮ፣ “ሳኦልንና ሳሙኤልን የማይከተል ሰው በሬው እንደዚህ ይቈራረጣል” ሲል በመላው እስራኤል አስነገረ። ታላቅ ፍርሀት ከእግዚአብሔር ዘንድ በሕዝቡ ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም እንደ አንድ ሰው ሆኖ ወጣ። ሳኦል ቤዜቅ በተባለ ስፍራ ሰራዊቱን በሰበሰበ ጊዜ፤ ቍጥራቸው ከእስራኤል ሦስት መቶ ሺሕ፣ ከይሁዳም ሠላሳ ሺሕ ነበር። ከዚያ ለመጡትም መልእክተኞች፣ “ለኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች፣ ‘ነገ ፀሓይ ሞቅ በሚልበት ጊዜ ነጻ ትሆናላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው” አሏቸው። መልእክተኞቹም ሄደው ለኢያቢስ ሰዎች ይህንኑ በነገሯቸው ጊዜ በደስታ ፈነደቁ። ለኢያቢስም ሰዎች፣ “እኛ ነገ እጃችንን እንሰጣችኋለን፤ እናንተም መልካም መስሎ የታያችሁን ሁሉ ልታደርጉብን ትችላላችሁ” አሏቸው። በማግስቱም ሳኦል ሰራዊቱን ከሦስት ቦታ ከፈለው፤ ሊነጋጋ ሲል፣ የአሞናውያንን ሰፈር ጥሰው በመግባት ፀሓይ ሞቅ እስኪል ድረስ ፈጇቸው። በሕይወት የተረፉትም ሁለት እንኳ ሆነው በአንድ ላይ ሊሆኑ እስከማይችሉ ድረስ ተበታተኑ። ሕዝቡ ሳሙኤልን፣ “ ‘ሳኦል እንዴት ሊገዛን ይችላል!’ ያሉት እነማን ነበሩ? እነዚህን ሰዎች እንገድላቸው ዘንድ አምጣቸው” አሉት። ሳኦል ግን፣ “ይህ ዕለት እግዚአብሔር እስራኤልን የታደገበት ቀን ስለ ሆነ፣ በዛሬው ዕለት ማንም ሰው አይገደልም” አለ። ከዚያም ሳሙኤል ሕዝቡን፣ “ኑና ወደ ጌልገላ እንሂድ፤ ንግሥናውን እናጽና” አለ። ሕዝቡ ሁሉ ወደ ጌልገላ ሄደ፤ የሳኦልንም ንጉሥነት በእግዚአብሔር ፊት አጸና። በዚያም ሕዝቡ የኅብረት መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ፤ ሳኦልና እስራኤላውያንም ሁሉ ታላቅ በዓል አደረጉ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}