ባሏ ሕልቃናም እርሷን፣ “ሐና ሆይ፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበዪም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከዐሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽምን?” ይላት ነበር። አንድ ጊዜ በሴሎ ሳሉ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሥታ ቆመች፤ በዚያ ጊዜ ካህኑ ዔሊ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መቃን አጠገብ በወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር። ሐናም በነፍሷ ተመርራ አብዝታ በማልቀስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች። እንዲህም ብላ ስእለት ተሳለች፤ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአገልጋይህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝና አገልጋይህን ሳትረሳት ወንድ ልጅ ብትሰጣት፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም።” ሐና ባለማቋረጥ ወደ እግዚአብሔር በጸለየች ጊዜ፣ ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር። እርሷም በልቧ ትጸልይ ስለ ነበር፤ ከንፈሯ ይንቀሳቀስ እንጂ ድምፅዋ አይሰማም ነበር፤ ዔሊም እንደ ሰከረች አድርጎ ቈጠራት። ዔሊም “ስካሩ የማይለቅሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አስወግጂው” አላት። ሐናም እንዲህ ብላ መለሰችለት፤ “ጌታዬ ሆይ፤ ሰክሬ አይደለም፤ እኔ ልቧ ክፉኛ የታወከባት ሴት ነኝ፤ ልቤን በእግዚአብሔር ፊት አፈሰስሁ እንጂ፣ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም። ይህን ያህል ጊዜ የጸለይሁት ከባድ ከሆነው ጭንቀቴና ሐዘኔ የተነሣ ስለ ሆነ፣ አገልጋይህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቍጠረኝ።” ዔሊም፣ “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሽውን ይስጥሽ” ሲል መለሰላት። እርሷም፣ “አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ታግኝ” አለች፤ ከዚያም መንገዷን ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ከዚያም በኋላ በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም። በማግስቱም ጧት ተነሥተው በእግዚአብሔር ፊት ሰገዱ፤ ከዚያም በራማ ወደሚገኘው ቤታቸው ሄዱ። ሕልቃና ከሚስቱ ከሐና ጋራ ተኛ፤ እግዚአብሔርም ዐሰባት፤ ስለዚህ ሐና ፀነሰች፤ የእርግዝናዋ ወራት በተፈጸመ ጊዜም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም፤ “ከእግዚአብሔር ለምኜዋለሁ” ስትል ሳሙኤል አለችው።
1 ሳሙኤል 1 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ሳሙኤል 1
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ሳሙኤል 1:8-20
9 ቀናት
የመጀመሪያው የሳሙኤል መጽሐፍ የእስራኤላዊት ሴት የሆነችውን የሐናን ታሪክ ይዘግባል። የሕይወቷ ሁኔታ ያስጎነበሳት እና ተስፋ አስቆራጭ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እሷን ምሳሌ የምትሆን ፈሪሃ አምላክ ያላት ሴት አድርጎ ይገልጻታል። ይህ የንባብ እቅድ የሐናን የህይወት ታሪክ ለራሳችን ህይወት እንደ ምሳሌ ይወስደዋል። ከእኛ ጋር ያንብቡ።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች