1 ጴጥሮስ 5
5
ለሽማግሌዎችና ለጕልማሶች የተሰጠ ምክር
1እንግዲህ ከእነርሱ ጋራ እኔም ሽማግሌና የክርስቶስ መከራ ምስክር የሆንሁ፣ እንዲሁም ወደ ፊት የሚገለጠው ክብር ተካፋይ የምሆን፣ በመካከላችሁ ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ፤ 2በእናንተ ኀላፊነት ሥር ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ የምትጠብቁትም ከእግዚአብሔር እንደሚጠበቅባችሁ በግድ ሳይሆን በፈቃደኝነት፣ ለጥቅም በመስገብገብ ሳይሆን ለማገልገል ባላችሁ ጽኑ ፍላጎት ይሁን፤ 3እንዲሁም በዐደራ ለተሰጣችሁ መንጋ መልካም ምሳሌ በመሆን እንጂ በላያቸው በመሠልጠን አይሁን። 4የእረኞች አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማይጠፋውን አክሊል ትቀበላላችሁ።
5ጕልማሶች ሆይ፤ እናንተም እንዲሁ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርስ በመከባበር ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም፣
“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤
ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”#5፥5 ምሳ 3፥34
6ስለዚህ እርሱ በወሰነው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከእግዚአብሔር ብርቱ እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ 7እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በርሱ ላይ ጣሉት።
8ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፣ ንቁም፤ ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራልና። 9በዓለም ዙሪያ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እንደሚቀበሉ ዐውቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።
10በክርስቶስ ኢየሱስ#5፥10 አንዳንድ ቅጆች ኢየሱስ የሚለው የላቸውም። ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ፣ ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ እርሱ ራሱ መልሶ ያበረታችኋል፤ አጽንቶም ያቆማችኋል። 11ኀይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ለርሱ ይሁን። አሜን።
የስንብት ሰላምታ
12እንደ ታማኝ ወንድም በምቈጥረው በሲላስ#5፥12 ወይም ስልዋኑስ አማካይነት ይህን ዐጭር መልእክት ጽፌላችኋለሁ፤ የጻፍሁላችሁም ልመክራችሁና ይህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ጸጋ መሆኑን ልመሰክርላችሁ ብዬ ነው። በዚህ ጸጋ ጸንታችሁ ቁሙ።
13ከእናንተ ጋራ የተመረጠችው፣ በባቢሎን የምትገኘው#5፥13 በአንዳንድ ጥንታዊ ቅጆች ላይ በባቢሎን የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ይላሉ። ሰላምታ ታቀርብላችኋለች፤ እንዲሁም ልጄ ማርቆስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል።
14በፍቅር አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ።
በክርስቶስ ላላችሁ ለሁላችሁ ሰላም ይሁን።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.