1 ጴጥሮስ 1:1-25

1 ጴጥሮስ 1:1-25 NASV

የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፤ በጳንጦስ፣ በገላትያ፣ በቀጰዶቅያ፣ በእስያና በቢታንያ ተበትነው በመጻተኛነት ለሚኖሩ ለእግዚአብሔር ምርጦች፤ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ካወቃቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝ በደሙ ለተረጩትና በመንፈስ አማካይነት ለተቀደሱት፤ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባትና አምላክ ይባረክ፤ እርሱ ከታላቅ ምሕረቱ የተነሣ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ምክንያት ለሕያው ተስፋ በሚሆን አዲስ ልደት፣ እንዲሁም በሰማይ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት እንደ ገና ወለደን። እናንተም በመጨረሻው ዘመን ሊገለጥ የተዘጋጀው ድነት እስኪመጣ ድረስ በእምነት አማካይነት በእግዚአብሔር ኀይል ተጠብቃችኋል። አሁን በብዙ ዐይነት ፈተና ውስጥ ሆናችሁ ለጥቂት ጊዜ መከራን ብትቀበሉም እንኳ በዚህ እጅግ ደስ ይላችኋል። እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ የደረሱት፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ፣ እውነተኛ መሆኑ እንዲረጋገጥና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን፣ ክብርንና ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው። እርሱንም ሳታዩት ትወድዱታላችሁ፤ አሁን ባታዩትም በርሱ ታምናላችሁ፤ መግለጽ በማይቻልና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ብሏችኋል፤ የእምነታችሁን ፍጻሜ፣ እርሱም የነፍሳችሁን ድነት እየተቀበላችሁ ነውና። ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ ድነት ተግተው በጥንቃቄ ይመረምሩ ነበር፤ በእነርሱ ውስጥ የነበረው የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ እንዲሁም ከመከራው በኋላ ስለሚሆነው ክብር አስቀድሞ በመናገር ያመለከታቸው ጊዜ መቼና እንዴት እንደሚፈጸም ይመረምሩ ነበር። አሁን ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ ወንጌልን ያበሠሩላችሁ ሰዎች የነገሯችሁን ነገር ባወሩላችሁ ጊዜ፣ እናንተን እንጂ ራሳቸውን እንዳላገለገሉ ተገለጠላቸው። መላእክትም እንኳ ሳይቀሩ እነዚህን ነገሮች ይመኛሉ። ስለዚህ ልባችሁን አዘጋጁ፤ ራሳችሁንም ግዙ፤ ተስፋችሁን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ ለእናንተ በሚሰጠው ጸጋ ላይ ሙሉ በሙሉ አድርጉ። ታዛዦች ልጆች እንደ መሆናችሁ መጠን ቀድሞ ባለማወቅ ትኖሩበት የነበረውን ክፉ ምኞት አትከተሉ። ነገር ግን የጠራችሁ እርሱ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ምክንያቱም “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” ተብሎ ተጽፏል። ለሰው ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደየሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ የምትጠሩት ከሆነ፣ በዚህ ምድር በእንግድነት ስትኖሩ በፍርሀት ኑሩ። ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ ከሆነ ሕይወት የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር፣ በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እናንተ የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው። እርሱ አስቀድሞ የታወቀው ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ሲሆን፣ አሁን ግን በመጨረሻው ዘመን ስለ እናንተ ተገለጠ። በርሱም አማካይነት፣ ከሞት ባስነሣውና ክብርን በሰጠው በእግዚአብሔር ታምናላችሁ፤ ስለዚህ እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው። እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን ስላነጻችሁ፣ ለወንድሞቻችሁ ቅን ፍቅር ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ። ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር ሳይሆን፣ ሕያው በሆነና ጸንቶ በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል አማካይነት ከማይጠፋ ዘር ነው። ምክንያቱም መጽሐፍ እንደሚል፣ “ሥጋ ለባሽ ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው። ሣሩ ይጠወልጋል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” የተሰበከላችሁም የምሥራች ቃል ይህ ነው።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}