1 ነገሥት 9:15-23

1 ነገሥት 9:15-23 NASV

ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ፣ የራሱን ቤተ መንግሥት፣ ሚሎን፣ የኢየሩሳሌምን ቅጥር፣ አሦርን፣ መጊዶንና ጌዝርን ለመሥራት የጕልበት ሠራተኞች መልምሎ ነበር። የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ወጥቶ በጌዝር ላይ አደጋ ጥሎ ያዛት፤ አቃጠላትም፤ ነዋሪዎቿን ከነዓናውያንን ገድሎ ለልጁ ለሰሎሞን ሚስት መዳሪያ አድርጎ ሰጥቷት ነበር፤ ሰሎሞንም ጌዝርን መልሶ ሠራት፤ እንዲሁም የታችኛውን ቤትሖሮንን፣ ባዕላትን፣ በይሁዳ ምድር በምድረ በዳው የምትገኘውን ተድሞርን ሠራ፤ በአጠቃላይ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም፣ በሊባኖስና በግዛቶቹ ሁሉ ለመሥራት የፈለጋቸውን ነገሮች፣ ዕቃ የሚከማችባቸውን ከተሞች፣ እንዲሁም ሠረገለኞችና ፈረሰኞች የሚቀመጡባቸውን ከተሞች ሁሉ ሠራ። እስራኤላውያን ያልሆኑትን ከአሞራውያን፣ ከኬጢያውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን የተረፉትን ሕዝቦች ሁሉ፣ እስራኤላውያን ዘሮቻቸውን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት ያልቻሉትንና በምድሪቱ የቀሩትን የእነዚህን ሕዝቦች ዘሮች እስከ ዛሬ ድረስ እንደሚደረገው የጕልበት ሥራ ይሠሩ ዘንድ ሰሎሞን መለመላቸው። ሰሎሞን ከእስራኤላውያን ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ ይልቁንም እነርሱ ወታደሮቹ፣ ሹማምቱ፣ የጦር አዛዦቹ፣ ሻምበሎቹ፣ የፈረሰኞችና የሠረገለኞች አዛዦቹ ነበሩ። እነዚህም ሰሎሞን የሚያሠራውን ሥራ የሚያከናውኑትን ሠራተኞች የሚቈጣጠሩ አለቆች ናቸው፤ ቍጥራቸውም ዐምስት መቶ ዐምሳ ነበር።