1 ነገሥት 8:1-21

1 ነገሥት 8:1-21 NASV

ከዚያም ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን እንዲያመጡ፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የእስራኤልን ነገድ አለቆችና የእስራኤልን ጐሣዎች ሹማምት ሁሉ፣ ንጉሡ ሰሎሞን ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። በዓሉ በሚከበርበት ኤታኒም በተባለው በሰባተኛው ወር፣ የእስራኤል ወንዶች ሁሉ ንጉሥ ሰሎሞን ወዳለበት ተሰበሰቡ። የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በመጡ ጊዜ፣ ካህናቱ ታቦቱን አነሡ፤ የእግዚአብሔርን ታቦት፣ የመገናኛውን ድንኳንና በውስጡ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አመጡ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ተሸከሟቸው። ንጉሥ ሰሎሞንና ዐብሮት በዚያ የተሰበሰበው መላው የእስራኤል ጉባኤ በታቦቱ ፊት ስፍር ቍጥር የሌላቸውን በጎችና በሬዎች ሠዉ። ከዚያም ካህናቱ የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት አምጥተው የቤተ መቅደሱ ውስጠኛ ክፍል ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ አግብተው ከኪሩቤል ክንፍ በታች ባለው ስፍራው አኖሩት። ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ከታቦቱ በላይ ባለው ስፍራ ላይ ዘርግተው፣ ታቦቱንና መሎጊያዎቹን ጋረዱ። መሎጊያዎቹ በጣም ከመርዘማቸው የተነሣ ጫፎቻቸው ከቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ካለው ከቅድስት ይታዩ ነበር፤ ከቅድስት ወዲያ ላለ ሰው ግን አይታዩም ነበር፤ እስከ ዛሬም ድረስ እዚያው ይገኛሉ። እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ በኋላ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋራ ኪዳን ባደረገ ጊዜ፣ ሙሴ በኮሬብ ተራራ በውስጡ ካስቀመጣቸው ከሁለቱ ጽላት በቀር በታቦቱ ውስጥ ምንም አልነበረም። ካህናቱ ከቤተ መቅደሱ በወጡ ጊዜ፣ ደመና የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሞላው። የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱን ሞልቶት ስለ ነበር፣ ከደመናው የተነሣ ካህናቱ አገልግሎታቸውን ማከናወን አልቻሉም። ከዚያም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ እንደሚኖር ተናግሯል፤ እነሆ፣ እኔም ለዘላለም የምትኖርበትን ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርቼልሃለሁ።” መላው የእስራኤል ጉባኤ በዚያ ቆሞ ሳለ፣ ንጉሡ ፊቱን ወደ እነርሱ መልሶ ጉባኤውን ባረከ። ከዚያም እንዲህ አለ፤ “ለአባቴ ለዳዊት በገዛ አፉ ተናግሮ የሰጠውን ተስፋ፣ እርሱ ራሱ በእጁ የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ እርሱም እንዲህ ብሎ ነበርና፤ ‘ሕዝቤን እስራኤልን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ዕለት አንሥቶ፣ ስሜ በዚያ እንዲጠራና ቤተ መቅደስ እንዲሠራበት ከመላው የእስራኤል ነገድ አንድም ከተማ አልመረጥሁም፤ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲመራ ግን ዳዊትን መረጥሁት።’ “አባቴ ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቡ ዐስቦ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፤ ‘ለስሜ ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልብህ ማሰብህ መልካም አድርገሃል፤ ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝ ከአብራክህ የሚከፈለው፣ የገዛ ልጅህ ነው።’ “እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል ፈጽሟል፤ እኔም እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔርም ስም ቤተ መቅደስ ሠርቻለሁ። ከግብጽ ባወጣቸው ጊዜ ከአባቶቻችን ጋራ የገባው የእግዚአብሔር ኪዳን በውስጡ ላለበት ታቦት መኖሪያ ስፍራ በዚያ አዘጋጅቻለሁ።”