1 ነገሥት 7:13-51

1 ነገሥት 7:13-51 NASV

ንጉሥ ሰሎሞንም መልእክተኛ ልኮ ኪራም የተባለውን ሰው ከጢሮስ አስመጣ፤ የኪራም እናት ከንፍታሌም ነገድ ስትሆን፣ እርሷም መበለት ነበረች፤ አባቱ የጢሮስ ሰው ሲሆን፣ የናስ ሥራ ባለሙያ ነበር። ኪራም በማናቸውም የናስ ሥራ ጥበብን፣ ማስተዋልንና ዕውቀትን የተሞላ ሰው ነበር፤ እርሱም ወደ ንጉሥ ሰሎሞን መጥቶ የተመደበለትን ሥራ ሁሉ አከናወነ። ኪራም የእያንዳንዱ ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ፣ ዙሪያው ዐሥራ ሁለት ክንድ የሆነ፣ ሁለት የናስ ምሰሶዎች ሠራ። እንዲሁም በምሰሶዎቹ ዐናት ላይ የሚሆኑ፣ ሁለት ጕልላት ከቀለጠ ናስ ሠራ፤ የእያንዳንዱም ጕልላት ቁመት ዐምስት ክንድ ነበር። በምሰሶዎቹ ዐናት ላይ ላሉት ጕልላቶችም ጌጥ እንዲሆኑ፣ ለእያንዳንዳቸው ሰባት የመረብ ሰንሰለት አበጀ፤ ደግሞም በምሰሶዎቹ ላይ ያሉትን ጕልላቶች ለማስጌጥ የእያንዳንዱን መረብ ዙሪያ የሚከብቡ ሮማኖች በሁለት ረድፍ ሠራ፤ ለሁለቱም ጕልላቶች ያደረገው ተመሳሳይ ነበር። በመመላለሻው ምሰሶዎች ዐናት ላይ ያሉት ጕልላቶች ቁመታቸው አራት ክንድ ሲሆን፣ የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበራቸው። በሁለቱም የምሰሶ ጕልላቶችና ከመርበቡ ቀጥሎ ባለው የክብ ቅርጽ ላይ ዙሪያውን በሙሉ ሁለት መቶ ሮማኖች በተርታ ነበሩ። ዐምዶቹንም በቤተ መቅደሱ መመላለሻ ላይ አቆመ፤ በስተ ደቡብ ያቆመውን ዐምድ “ያኪን”፣ በስተሰሜን በኩል ያለውንም “ቦዔዝ” ብሎ ጠራው። ዐናቱ ላይ ያሉት ጕልላቶች የሱፍ አበባ ቅርጽ ነበራቸው። የምሰሶዎቹም ሥራ በዚህ ሁኔታ ተፈጸመ። ቅርጹ ክብ፣ ስፋቱ ከጠርዝ እስከ ጠርዝ ዐሥር ክንድ፣ ቁመቱ ዐምስት ክንድ የሆነ ክብ ገንዳ ከቀለጠ ብረት ሠራ፤ ዙሪያውም ሲለካ ሠላሳ ክንድ ሆነ። ከገንዳው ከንፈር በታችም፣ በእያንዳንዱ ክንድ ላይ እንደ ቅል ያሉ ዐሥር ቅርጾች ዙሪያውን በሁለት ረድፍ ከብበውታል፤ እነዚህም ከገንዳው ጋራ አንድ ወጥ ሆነው በሁለት ረድፍ ተሠርተው ነበር። ገንዳውም፣ ሦስቱ ፊታቸውን ወደ ሰሜን፣ ሦስቱ ወደ ደቡብ፣ ሦስቱ ወደ ምዕራብ፣ ሦስቱ ወደ ምሥራቅ ባዞሩ የዐሥራ ሁለት በሬዎች ምስሎች ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ገንዳው በላያቸው ሆኖ የሁሉም የኋላ አካል በመካከል ላይ የገጠመ ነበር። የገንዳው ውፍረት አንድ ስንዝር ሲሆን፣ የከንፈሩ ጠርዝ ደግሞ የአበባ ቅርጽ ያለው የጽዋ ከንፈር የመሰለ ነው፤ ይህም ሁለት ሺሕ የባዶስ መስፈሪያ ያህል ውሃ የሚይዝ ነበር። እንዲሁም ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ዐሥር ባለመንኰራኵር የዕቃ ማስቀመጫዎች ከመዳብ ሠራ፤ የእያንዳንዱም ርዝመት አራት ክንድ፣ ወርድ አራት ክንድ፣ ቁመትም ሦስት ክንድ ነበር። የዕቃ ማስቀመጫዎቹ የተሠሩት እንደዚህ ነው፤ እነዚህም ቀጥ ብለው ከቆሙ ደጋፊዎች ጋራ የተያያዙ ባለአራት ማእዘን ጠፍጣፋ ናሶች ነበሯቸው። ዳርና ዳር ባሉት ድጋፎች መካከል በሚገኙት ጠፍጣፋ ናሶች ላይ የአንበሶችን፣ የኰርማዎችንና የኪሩቤልን ምስል አደረገ፤ በድጋፎቹም ላይ እንደዚሁ አደረገ። ከአንበሶቹና ከኰርማዎቹ በላይና በታች በኩል ደግሞ የአበባ ጕንጕን የሚመስሉ ተቀጥቅጠው የተሠሩ ቅርጾች ነበሩ። እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት የናስ መንኰራኵርና መንኰራኵሮቹ የሚሽከረከሩባቸው የናስ ወስከምቶች እንዲሁም እያንዳንዳቸው በአራቱም ማእዘን ገጽ ላይ የአበባ ጕንጕን ቀልጦ የተሠራባቸው የመታጠቢያ ገንዳ መደገፊያዎች ነበረው። በዕቃ ማስቀመጫዎቹም ውስጥ ጥልቀቱ አንድ ክንድ የሆነ ባለክብ ክፍተት ነበር፤ ይህም ክፍተት ድቡልቡል ሆኖ ከታች ከመቆሚያው በኩል ደግሞ አንድ ክንድ ተኩል ወርድ ሲኖረው፣ በክፍተቱም ዙሪያ ቅርጾች ነበሩ፤ ክፈፎቹ ግን ባለአራት ማእዘን እንጂ ክብ አልነበሩም። አራቱ መንኰራኵሮች በዕቃ ማስቀመጫው ጠፍጣፋ ናስ ሥር ሲሆኑ፣ የመንኰራኵሮቹ ወስከምቶች ደግሞ ከዕቃ ማስቀመጫዎቹ ጋራ የተያያዙ ነበሩ፤ የእያንዳንዱም መንኰራኵር ስፋት አንድ ክንድ ተኩል ነበር። መንኰራኵሮቹ የሠረገላ መንኰራኵር መሰል ሲሆኑ፣ ወስከምቶቹ የመንኰራኵሮቹ ክፈፎችና ዐቃፊዎቻቸው እንዲሁም ወስከምቶቹ የሚገቡባቸው ቧንቧዎች በሙሉ ከቀለጠ ብረት የተሠሩ ነበሩ። እያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ አራት ወጣ ያለ እጀታ ነበረው። በዕቃ ማስቀመጫው ጫፍ ላይ ግማሽ ክንድ የሆነ ዙሪያ ክብ ነበረበት፤ ድጋፎቹና ጠፍጣፋ ናሶቹ ከዕቃ ማስቀመጫው ዐናት ጋራ የተያያዙ ነበሩ። እርሱም በድጋፎቹና በጠፍጣፋ ናሶቹ ላይ ባለው ቦታ ሁሉ፣ ዙሪያውን የአበባ ጕንጕን እያደረገ ኪሩቤልን፣ አንበሶችንና የዘንባባ ዛፎችን ቀረጸ። ዐሥሩም የዕቃ ተሸካሚዎች የተሠሩት በዚህ ሁኔታ ነበር፤ ሁሉም ከአንድ ቅርጽ ቀልጠው የወጡ ስለ ሆነ፣ በመጠንና በቅርጽ ፍጹም ተመሳሳይ ነበሩ። ከዚያም ለእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ የሚሆን፣ እያንዳንዱ አርባ የባዶስ መስፈሪያ የሚይዝ ዐሥር የናስ መታጠቢያ ገንዳ ሠራ፤ ስፋቱም አራት ክንድ ነበር። ከዕቃ ማስቀመጫዎቹም ዐምስቱን ከመቅደሱ በስተ ደቡብ፣ ዐምስቱን በስተሰሜን በኩል አኖረ፤ ገንዳውንም ከቤተ መቅደሱ በደቡብ ምሥራቅ ጫፍ ላይ በስተ ደቡብ አኖረው። ኪራምም ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን ሠራ። ኪራምም ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ለንጉሥ ሰሎሞን የሠራውን ሥራ ሁሉ ፈጸመ እነዚህም፦ ሁለቱን አዕማድ፣ በአዕማዱ ጫፎች ላይ ያሉትን ሁለት ባለሳሕን ጕልላቶችን፤ በአዕማዱ ላይ ያሉትን ባለሳሕን ቅርጽ ሁለት ጕልላቶችን ያስጌጡትን ሁለት መረቦች፤ በአዕማዱ ጫፎች ላይ ያሉትን ባለሳሕን ቅርጽ ጕልላቶች የሚሸፍኑና በሁለት ረድፍ የተቀረጹትን መረቦች የሚያስጌጡትን አራት መቶ ሮማኖች፤ ዐሥሩን የዕቃ ማስቀመጫዎች፣ ከዐሥር መታጠቢያ ገንዳዎቻቸው ጋራ፤ ገንዳውና ከሥሩ ያሉትን ዐሥራ ሁለት ኰርማዎች፤ ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችን እና ጐድጓዳ ሳሕኖችን። ኪራም ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ እንዲሆኑ እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ ለንጉሥ ሰሎሞን የሠራለት ከሚብረቀረቅ ናስ ነበር። ንጉሡም እነዚህ ዕቃዎች በዮርዳኖስ ሸለቆ፣ በሱኮትና በጻርታን መካከል ባለው በሸክላ ዐፈር ቦታ ቀልጠው በሸክላ ቅርጽ ተሠርተው እንዲወጡ አደረገ። ሰሎሞን ከብዛታቸው የተነሣ እነዚህ ሁሉ ዕቃዎች እንዲመዘኑ አላደረገም፣ ስለዚህም የናሱ ክብደት ምን ያህል እንደ ነበር አልታወቀም። እንደዚሁም ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ የሚሆኑትን ዕቃዎች ሠራ፤ እነዚህም፦ የወርቅ መሠዊያ፣ የገጸ ኅብስቱ ጠረጴዛ፣ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ዐምስቱ በቀኝ፣ ዐምስቱ በግራ የሚቀመጡ፣ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ መቅረዞችን፣ ከወርቅ የተቀረጹ አበቦችን፣ ቀንዲሎችንና መኰስተሪያዎችን፤ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ጽዋዎችን፣ የመብራት መኰስተሪያዎችን፣ ለመርጫ የሚሆኑ ጐድጓዳ ሳሕኖችን፣ ጭልፋዎችን፣ የዕጣን ማቅረቢያ ዕቃዎችን፣ ለውስጠኛው ክፍል ለቅድስተ ቅዱሳኑ በሮችና እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ በሮች የሚሆኑ የወርቅ ማጠፊያዎችን። ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሠራው ሥራ ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ አባቱ ዳዊት የቀደሰውን ብሩንና ወርቁን፣ ዕቃዎቹንም ሁሉ አምጥቶ በእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት አኖራቸው።