ሰሎሞን የራሱን ቤተ መንግሥት ሠርቶ ለመጨረስ ዐሥራ ሦስት ዓመት ፈጀበት። የሊባኖስ ዱር የተባለ ቤተ መንግሥት ሠራ፤ ይህም ርዝመቱ መቶ ክንድ፣ ወርዱ ዐምሳ ክንድ፣ ቁመቱ ሠላሳ ክንድ ሲሆን፣ በአራት ረድፍ የቆሙ የዝግባ ምሰሶዎች ደግፈው የያዟቸው አግዳሚ የዝግባ ተሸካሚዎች ነበሩት። ቤቱ ከምሰሶዎቹ ላይ ያረፉ አግዳሚ ተሸካሚዎች አሉት፤ በእያንዳንዱ ዐምድ ላይ ዐሥራ ዐምስት፣ በድምሩ አርባ ዐምስት ተሸጋጋሪዎች ሲኖሩ፣ ከእነዚህም ተሸጋጋሪዎች በላይ ከዝግባ የተሠራ የጣሪያ ክዳን ነበር። መስኮቶቹም ከፍ ብለው የተሠሩ በሦስት ምድብ የተከፈሉና ትይዩ ነበሩ። በሮቹ በሙሉ ባለአራት ማእዘን መቃኖች ያሏቸው፣ በሦስት ምድብ የተከፈሉና ትይዩ ነበሩ። ሰሎሞን፣ “ባለብዙ ምሰሶ አዳራሽ” የተባለ ቤት ሠራ፤ የዚህም ርዝመቱ ዐምሳ ክንድ፣ ወርዱ ሠላሳ ክንድ፣ ነበር፤ በስተ ፊት በኩልም ጣራ ያለውና በአዕማድ የተደገፈ መመላለሻ ነበረው። ዳኝነት የሚያይበትንም የዙፋን ችሎት አዳራሽ ሠራ፤ ይኸውም የፍትሕ አዳራሽ የተባለው ነው፤ ይህንም ከወለሉ አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ ሳንቃ ሸፈነው። ከአዳራሹ በስተጀርባ ባለው አደባባይ መኖሪያው እንዲሆን የተሠራው ቤተ መንግሥትም የዚሁ ተመሳሳይ ነበር። ሰሎሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ይህንኑ ቤተ መንግሥት የመሰለ አዳራሽ ሠራ። ከውጭ አንሥቶ እስከ ትልቁ አደባባይ፣ ከመሠረቱ አንሥቶ እስከ ድምድማቱ ያለው የሕንጻ ሥራ በሙሉ፣ በውስጥም በውጭም በልክ በልኩ በተቈረጠና አምሮ በተጠረበ ምርጥ ድንጋይ የተሠራ ነበር። መሠረቱም ዐሥርና ስምንት ክንድ ርዝመት ባላቸውና ምርጥ በሆኑ ታላላቅ ድንጋዮች የተሠራ ነበር። በላዩም ላይ ምርጥ የሆኑ፣ በልክ በልኩ የተቈረጡ ድንጋዮችና የዝግባ ሳንቃዎች ነበሩ። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጠኛ አደባባይ ከመመላለሻ በረንዳው ጭምር እንደ ትልቁ አደባባይ አምሮ በተጠረበ ሦስት ረድፍ ድንጋይና ተስተካክሎ በተከረከመ በአንድ ረድፍ የዝግባ ሳንቃ የታጠረ ነበር።
1 ነገሥት 7 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ነገሥት 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ነገሥት 7:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች