1 ነገሥት 22:41-50

1 ነገሥት 22:41-50 NASV

የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በነገሠ በአራተኛው ዓመት የአሳ ልጅ ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ነገሠ። ኢዮሣፍጥ መንገሥ በጀመረ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዐምስት ዓመት ነበረ፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ ሃያ ዐምስት ዓመት ገዛ። እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች። እርሱም በአካሄዱ ሁሉ የአባቱን የአሳን መንገድ ተከተለ፤ ከዚያም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት መልካም የሆነውን አደረገ፤ ይሁን እንጂ በየኰረብታው ላይ ያሉት የማምለኪያ ስፍራዎች ገና አልተወገዱም፤ ሕዝቡም በዚያ መሥዋዕት ማቅረቡንና ዕጣን ማጤሱን እንደ ቀጠለ ነበር። እንዲሁም ኢዮሣፍጥ ከእስራኤል ንጉሥ ጋራ በሰላም ኖረ። የቀረውም ኢዮሣፍጥ በዘመነ መንግሥቱ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ያከናወናቸው ተግባራት፦ ጀግንነቱና ያደረጋቸው ጦርነቶች ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፉ አይሉምን? ከአባቱ ከአሳ ዘመን በኋላ እንኳ ተርፈው በጣዖት ማምለኪያ ቦታዎች የነበሩትን የወንደቃ ቅሬታዎች ከምድሪቱ አስወገደ። በዚያ ጊዜ ኤዶም ንጉሥ አልነበራትም፤ የሚገዛት እንደራሴ ነበር። ኢዮሣፍጥ ወርቅ ለማምጣት ወደ ኦፊር የሚሄዱ የተርሴስ መርከቦች አሠርቶ ነበር፤ ይሁን እንጂ በዔጽዮንጋብር ስለ ተሰበሩ ከቶ ወደዚያ መሄድ አልቻሉም ነበር። በዚያ ጊዜም የአክዓብ ልጅ አካዝያስ ኢዮሣፍጥን “ሰዎቼ ከሰዎችህ ጋራ በመርከብ ይሂዱ” ሲል ጠይቆት ነበር፤ ኢዮሣፍጥ ግን ዕሺ አላለውም። ኢዮሣፍጥ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበት በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ኢዮራምም በምትኩ ነገሠ።