የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም በይሁዳ ነገሠ፤ በነገሠም ጊዜ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመት ነበር፤ እርሱም እግዚአብሔር ስሙን በዚያ ለማኖር ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጣት በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀምጦም ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ። እናቱም ናዓማ የተባለች አሞናዊት ነበረች። ይሁዳ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ከአባቶቻቸው ይልቅ እነርሱ በሠሩት ኀጢአት ይበልጥ የቅናት ቍጣውን አነሣሡ፤ እንዲሁም በእያንዳንዱ ኰረብታና በየትልልቁ ዛፍ ጥላ ሥር የማምለኪያ ኰረብቶችን አዕማደ ጣዖታት፣ የአሼራን ምስል ዐምድ ለራሳቸው አቆሙ። ከዚያም ይልቅ፣ የቤተ ጣዖት ወንደቃዎች በምድሪቱ ላይ ነበሩ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት አሳድዶ ያስወጣቸው አሕዛብ የፈጸሙትን አስጸያፊ ድርጊት ሁሉ እነዚህም ፈጸሙ። ሮብዓም በነገሠ በዐምስተኛው ዓመት፣ የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ ዘመተ፤ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ንብረትና የቤተ መንግሥቱን ንብረት ዘርፎ ወሰደ፤ ሰሎሞን ያሠራው የወርቅ ጋሻ፤ ሰሎሞን ያሠራቸው የወርቅ ጋሻዎች ሁሉ እንኳ ሳይቀሩ ሁሉንም ነገር አጋዘ። ስለዚህ ንጉሥ ሮብዓም እነዚህን ለመተካት ሲል፣ የናስ ጋሻዎች ሠርቶ የቤተ መንግሥቱን ቅጥር በር ለሚጠብቁ የዘብ አለቆች በኀላፊነት ሰጠ። ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በሚሄድበት ጊዜ ሁሉ፣ ዘቦቹ ጋሻዎቹን አንግበው ያጅቡት ነበር፤ ከዚያም በዘብ ጥበቃው ክፍል መልሰው ያስቀምጡ ነበር። የቀረው የሮብዓም አገዛዝ፣ ያደረገውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል የማያቋርጥ ጦርነት ነበር።
1 ነገሥት 14 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ነገሥት 14
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ነገሥት 14:21-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች