ከዚያም ኢዮርብዓም በኰረብታው አገር በኤፍሬም የምትገኘውን ሴኬምን ምሽግ አድርጎ ሠራ፤ በዚያም ተቀመጠ። ደግሞም ያን ትቶ በመውጣት የጵኒኤልን ምሽግ ሠራ። ኢዮርብዓም በልቡ እንዲህ ሲል ዐሰበ፤ “መንግሥቱ ለዳዊት ቤት የሚመለስ ይመስላል፤ ይህ ሕዝብ መሥዋዕት ለማቅረብ ኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚወጣ ከሆነ፣ እንደ ገና ልቡን ወደ ጌታው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሮብዓም ሊያዞር ነው። ከዚያም እኔን ይገድለኛል፤ ወደ ንጉሡም ወደ ሮብዓም ይመለሳል።” ንጉሡ ከመከረበት በኋላ ሁለት የወርቅ ጥጆች አሠርቶ ሕዝቡን፣ “እስራኤል ሆይ፤ ወደ ኢየሩሳሌም እስካሁን የወጣኸው ይበቃል፤ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው” አለ። አንዱን በቤቴል ሌላውንም በዳን አቆመው። ይህም አድራጎት ኀጢአት ሆነ፤ ሕዝቡም በዚያ ላለው ለመስገድ እስከ ዳን ድረስ ርቆ ሄደ። ኢዮርብዓም በማምለኪያ ኰረብቶች ላይ አብያተ ጣዖታትን ሠራ፤ ከሕዝቡ የተለያዩ ክፍሎች ሁሉ፣ ሌዋውያን ካልሆኑት ካህናትን ሾመ። በይሁዳ እንደሚደረገው ሁሉ ኢዮርብዓምም በስምንተኛው ወር ዐሥራ ዐምስተኛው ቀን በዓል እንዲሆን ወሰነ፤ በመሠዊያውም ላይ መሥዋዕት አቀረበ። ለሠራቸው ጥጆች መሥዋዕት በማቅረብም እንዲህ ያለውን ድርጊት በቤቴል ፈጸመ። በማምለኪያ ኰረብቶች ላይ ላሠራቸው አብያተ ጣዖታት በቤቴል ካህናቱን መደበ። ራሱ በመረጠው በስምንተኛው ወር፣ በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን በቤቴል ባቆመው መሠዊያ ላይ መሥዋዕት አቀረበ፤ ስለዚህ ለእስራኤላውያን በዓል ወሰነላቸው፤ ዕጣንም ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ወጣ።
1 ነገሥት 12 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ነገሥት 12
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ነገሥት 12:25-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች