እስራኤላውያን ሁሉ ሊያነግሡት ወደ ሴኬም መጥተው ስለ ነበር፣ ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ። ከንጉሥ ሰሎሞን ሸሽቶ በግብጽ ይኖር የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን ሲሰማ፣ ከግብጽ ተመልሶ መጣ። እርሱንም ልከው አስጠሩት፤ ከዚያም እርሱና እስራኤል ሁሉ ወደ ሮብዓም መጥተው፣ እንዲህ አሉት፤ “አባትህ ቀንበራችንን አከበደብን፤ አንተ ግን አሁን አስጨናቂውን ሥራና በላያችን የጫነብንን ከባድ ቀንበር አቅልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን” አሉት። ሮብዓምም፣ “ሂዱ፤ ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ” አላቸው። ስለዚህ ሰዎቹ ወጥተው ሄዱ። ከዚያም ንጉሡ ሮብዓም አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ ካገለገሉት ሽማግሌዎች ጋራ ተማከረ፤ “ለዚህ ሕዝብ ምን መልስ እንድሰጥ ትመክሩኛላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “ዛሬ አንተ ለዚህ ሕዝብ አገልጋይ ብትሆን፣ ብትገዛለትና ደስ የሚያሰኝ መልስ ብትሰጠው፣ ምን ጊዜም አገልጋይህ ይሆናል” ብለው መለሱለት። ሮብዓም ግን ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ንቆ፣ ዐብሮ አደጎቹንና በፊቱ ቆመው የሚያገለግሉትን ወጣቶች ምክር ጠየቀ፤ እንዲህም አላቸው፤ “ ‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን’ ለሚሉኝ ለእነዚህ ሰዎች የምትሰጡኝ ምክር ምንድን ነው? ምንስ ብለን እንመልስላቸው?” ዐብሮ አደጎቹም ወጣቶች እንዲህ አሉት፤ “ ‘አባትህ በላያችን ከባድ ቀንበር ጫነብን፣ አንተ ግን ቀንበራችንን አቅልልልን’ ለሚሉህ ለእነዚህ ሰዎች፣ ‘ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ይልቅ ትወፍራለች፤ አባቴ ከባድ ቀንበር ጫነባችሁ፤ እኔ ግን የባሰ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በዐለንጋ ገረፋችሁ፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ።’ ” ንጉሡ፣ “በሦስተኛው ቀን ተመልሳችሁ ኑ” ባላቸው መሠረት፣ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም ተመልሰው መጡ። ንጉሡም በሽማግሌዎቹ የተሰጠውን ምክር ንቆ ሕዝቡን የሚያስከፋ መልስ ሰጣቸው፤ እርሱም ወጣቶቹ በሰጡት ምክር መሠረት፣ “አባቴ ቀንበራችሁን አከበደባችሁ፤ እኔ ደግሞ የባሰ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በዐለንጋ ገረፋችሁ፣ እኔ ደግሞ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” አላቸው። እግዚአብሔር በሴሎናዊው በአኪያ አማካይነት ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ስለ ወሰነ፣ ንጉሡ ሕዝቡን አላዳመጠም። መላው እስራኤልም ንጉሡ ሊሰማቸው አለመፈለጉን በተረዱ ጊዜ፣ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ከዳዊት ምን ድርሻ አለን? ከእሴይስ ልጅ ምን ክፍል አለን? እስራኤል፣ ሆይ፤ ወደ ድንኳንህ ተመለስ፤ ዳዊት ሆይ፤ አንተም የገዛ ቤትህን ጠብቅ።” ስለዚህ እስራኤላውያን ወደ የቤታቸው ተመለሱ። ይሁን እንጂ ሮብዓምም በይሁዳ ከተሞች በሚኖሩት እስራኤላውያን ላይ ነገሠ። ንጉሥ ሮብዓም የጕልበት ሠራተኞች አለቃ የነበረውን አዶኒራምን ላከው፤ ነገር ግን እስራኤል ሁሉ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሡ ሮብዓም ግን እንደ ምንም ብሎ ሠረገላው ላይ በመውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ። ስለዚህ እስራኤል እስከ ዛሬ ድረስ በዳዊት ቤት ላይ እንዳመፀ ነው። ኢዮርብዓም መመለሱን እስራኤላውያን ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣ ወደ ጉባኤያቸው በማስጠራት በመላው እስራኤል ላይ አነገሡት። ለዳዊት ቤት በታማኝነት ጸንቶ የተገኘው የይሁዳ ቤት ብቻ ነው። ሮብዓም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ፣ የእስራኤልን ቤት ወግተው መንግሥቱን ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም እንዲመልሱ መላውን የይሁዳ ቤትና የብንያምን ነገድ ሰበሰበ፤ የሰራዊቱም ቍጥር አንድ መቶ ሰማንያ ሺሕ ነበር። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል፣ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ሆነው ወደ ሸማያ እንዲህ ሲል መጣ፤ “ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም፣ ለመላው ይሁዳና ብንያም፣ ለቀረውም ሕዝብ ሁሉ እንዲህ በል፤ ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ይህ ነገር ከእኔ የሆነ ነውና ወንድሞቻችሁን እስራኤላውያንን ለመውጋት አትውጡ፤ እያንዳንዳችሁ ወደየቤታችሁ ተመለሱ።’ ” ስለዚህ እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ፤ ወደየቤታቸውም ተመለሱ።
1 ነገሥት 12 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ነገሥት 12
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ነገሥት 12:1-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች