1 ዮሐንስ 3:10-18

1 ዮሐንስ 3:10-18 NASV

የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፤ ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። ከመጀመሪያ የሰማችኋት፣ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል የምትለዋ መልእክት ይህች ናትና፤ የክፉው ወገን ሆኖ ወንድሙን እንደ ገደለው እንደ ቃየን አትሁኑ፤ ለምን ገደለው? ምክንያቱም የርሱ ሥራ ክፉ፣ የወንድሙ ግን ጽድቅ ስለ ነበረ ነው። ወንድሞች ሆይ፤ ዓለም ቢጠላችሁ አትደነቁ። ወንድሞቻችንን ስለምንወድድ ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ፍቅር የሌለው ሁሉ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይም የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ። ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ ስለ ሰጠ፣ ፍቅር ምን እንደ ሆነ በዚህ እናውቃለን፤ እኛም ሕይወታችንን ስለ ወንድሞቻችን አሳልፈን ልንሰጥ ይገባናል። ማንም የዚህ ዓለም ሀብት እያለው፣ ወንድሙ ሲቸገር አይቶ ልቡ ባይራራለት፣ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት በርሱ ይኖራል? ልጆች ሆይ፤ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።