1 ዮሐንስ 3:1-12

1 ዮሐንስ 3:1-12 NASV

የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንድንጠራ አብ አትረፍርፎ ያፈሰሰልን ፍቅር ምንኛ ታላቅ ነው! እኛም እንዲሁ ልጆቹ ነን። ዓለም እኛን የማያውቀንም እርሱን ስላላወቀው ነው። ወዳጆች ሆይ፤ እኛ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች ነን፤ ወደ ፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። እርሱ በሚገለጥበት ጊዜ እናየዋለን፤ እርሱን እንደምንመስልም እናውቃለን። በርሱ ይህን ተስፋ የሚያደርግ ሁሉ፣ እርሱ ንጹሕ እንደ ሆነ ራሱን ያነጻል። ኀጢአት የሚያደርግ ሁሉ ዐመፅን ያደርጋል፤ ኀጢአትም ዐመፅ ነው። እርሱ ኀጢአትን ሊያስወግድ እንደ ተገለጠ ታውቃላችሁ፤ በርሱም ኀጢአት የለም። በርሱም የሚኖር ኀጢአትን አያደርግም፤ ኀጢአት የሚያደርግ ግን እርሱን አላየውም ወይም አላወቀውም። ልጆች ሆይ፤ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ፣ ጽድቅን የሚያደርግ ጻድቅ ነው። ኀጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፤ ምክንያቱም ዲያብሎስ ከመጀመሪያ አንሥቶ ኀጢአትን የሚያደርግ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የተገለጠውም የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ ነው። ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኀጢአትን በመለማመድ አይቀጥልም፤ የርሱ ዘር በውስጡ ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደም ኀጢአትን ሊያደርግ አይችልም። የእግዚአብሔር ልጆችና የዲያብሎስ ልጆች ተለይተው የሚታወቁት በዚህ ነው፤ ጽድቅን የማያደርግ፣ ወንድሙንም የማይወድድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም። ከመጀመሪያ የሰማችኋት፣ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል የምትለዋ መልእክት ይህች ናትና፤ የክፉው ወገን ሆኖ ወንድሙን እንደ ገደለው እንደ ቃየን አትሁኑ፤ ለምን ገደለው? ምክንያቱም የርሱ ሥራ ክፉ፣ የወንድሙ ግን ጽድቅ ስለ ነበረ ነው።