ልጆቼ ሆይ፤ ይህን የምጽፍላችሁ ኀጢአት እንዳትሠሩ ነው፤ ነገር ግን ማንም ኀጢአት ቢሠራ፣ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን፤ እርሱም ጻድቁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኀጢአታችን ማስተስረያ ነው፤ ይኸውም ለዓለም ሁሉ ኀጢአት እንጂ ለእኛ ብቻ አይደለም። ትእዛዞቹን ብንፈጽም እርሱን ማወቃችንን በዚህ ርግጠኞች እንሆናለን። “እርሱን ዐውቃለሁ” እያለ ትእዛዞቹንም የማይፈጽም ግን ሐሰተኛ ነው፤ እውነቱም በርሱ ውስጥ የለም። ነገር ግን ማንም ቃሉን ቢጠብቅ፣ በእውነት የእግዚአብሔር ፍቅር በርሱ ፍጹም ሆኗል። በርሱ መሆናችንን የምናውቀው በዚህ ነው፤ ማንም በርሱ እኖራለሁ የሚል፣ ኢየሱስ እንደ ተመላለሰ ሊመላለስ ይገባዋል። ወዳጆች ሆይ፤ የምጽፍላችሁ፣ ከመጀመሪያ የነበራችሁን የቈየውን ትእዛዝ እንጂ አዲስ ትእዛዝ አይደለም፤ የቈየው ትእዛዝ የሰማችሁት ቃል ነው። በሌላ በኩል የምጽፍላችሁ ጨለማው እያለፈና እውነተኛው ብርሃን እየበራ ስለ ሆነ፣ በርሱም፣ በእናንተም ዘንድ እውነት የሆነውን አዲስ ትእዛዝ ነው። በብርሃን አለሁ የሚል፣ ወንድሙን ግን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ። ወንድሙን የሚወድድ በብርሃን ይኖራል፤ በርሱም ዘንድ የመሰናከያ ምክንያት የለውም። ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል፤ ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም። ልጆች ሆይ፤ ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ። አባቶች ሆይ፤ ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ። ጐበዛዝት ሆይ፤ ክፉውን አሸንፋችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ። ልጆች ሆይ፤ አብን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ። አባቶች ሆይ፤ ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ። ጐበዛዝት ሆይ፤ ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ፣ የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ስለሚኖር፣ ክፉውንም ስላሸነፋችሁ፣ እጽፍላችኋለሁ።
1 ዮሐንስ 2 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ዮሐንስ 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ዮሐንስ 2:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች