1 ቆሮንቶስ 8:1-13

1 ቆሮንቶስ 8:1-13 NASV

ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋ ደግሞ ይህን እላለሁ፤ ሁላችንም ዕውቀት እንዳለን እናውቃለን። ዕውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል። ዐውቃለሁ የሚል ሰው፣ ማወቅ የሚገባውን ያህል ገና አላወቀም። እግዚአብሔርን የሚወድድ ሰው ግን በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው። እንግዲህ፣ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ ስለ መብላት፣ በዚህ ዓለም ጣዖት ከንቱ እንደ ሆነና ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። መቼም ብዙ “አማልክትና” ብዙ “ጌቶች” አሉ፤ በሰማይም ሆነ በምድር አምላክ ተብለው የሚጠሩ አማልክት ቢኖሩም፣ ለእኛ ግን ሁሉም ነገር ከርሱ የሆነ፣ እኛም ለርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፤ ደግሞም ሁሉም ነገር በርሱ አማካይነት የሆነ፣ እኛም በርሱ አማካይነት የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን። ነገር ግን ይህን የሚያውቁ ሁሉም አይደሉም፤ አንዳንድ ሰዎች እስከ አሁን ድረስ ጣዖትን ማምለክ ስለ ለመዱ፣ እንዲህ ያለውን ሥጋ ሲበሉ በርግጥ ለጣዖት እንደ ተሠዋ ያስባሉ፤ ኅሊናቸውም ደካማ ስለ ሆነ ይረክሳል። ነገር ግን ምግብ ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ባንበላ የሚጐድልብን ነገር የለም፤ ብንበላም የምናተርፈው ነገር አይኖርም። ነገር ግን ከነጻነታችሁ የተነሣ የምታደርጉት ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆን ተጠንቀቁ። አንተ ይህን የመሰለ ዕውቀት ኖሮህ፣ ደካማ ኅሊና ያለው ሰው በቤተ ጣዖት ስትበላ ቢያይህ፣ ለጣዖት የተሠዋውን ምግብ ለመብላት አይደፋፈርምን? ስለዚህ ክርስቶስ የሞተለት ይህ ደካማ ወንድም በአንተ ዕውቀት ምክንያት ጠፋ ማለት ነው። በዚህ መንገድ ወንድሞቻችሁን በመበደልና ደካማ ኅሊናቸውን በማቍሰል፣ ክርስቶስን ትበድላላችሁ። ስለዚህ እኔ የምበላው ነገር ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፣ ወንድሜን ላለማሰናከል ስል ከቶ ሥጋ አልበላም።