1 ቆሮንቶስ 7:1-40

1 ቆሮንቶስ 7:1-40 NASV

ስለ ጻፋችሁልኝ ጕዳይ፣ ሰው ወደ ሴት ባይደርስ መልካም ነው፤ ነገር ግን ከዝሙት ለመጠበቅ፣ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ሚስት ትኑረው፤ እያንዳንዷም ሴት የራሷ ባል ይኑራት። ባል ለሚስቱ የሚገባትን ሁሉ ያድርግላት፤ ሚስትም ለባሏ እንዲሁ። ሚስት በራሷ አካል ላይ ሥልጣን የላትም፤ ባሏ እንጂ። እንዲሁም ባል በራሱ አካል ላይ ሥልጣን የለውም፤ ሚስቱ እንጂ። በጸሎት ለመትጋት ተስማምታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ካልሆነ በቀር፣ እርስ በርሳችሁ አትከላከሉ፤ ራሳችሁን ባለመግዛት ሰይጣን እንዳይፈታተናችሁ እንደ ገና ዐብራችሁ ሁኑ። ይህን የምለው ግን እንደ ትእዛዝ ሳይሆን እንደ ምክር ነው። ሰው ሁሉ እንደ እኔ ቢሆን ምኞቴ ነው። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ከእግዚአብሔር የተቀበለው የራሱ የሆነ ስጦታ አለው፤ አንዱ አንድ ዐይነት ስጦታ ሲኖረው፣ ሌላው ደግሞ ሌላ ዐይነት ስጦታ አለው። ላላገቡና ባሎቻቸው ለሞቱባቸው ሴቶች ግን እንዲህ እላለሁ፤ ሳያገቡ እንደ እኔ ቢኖሩ ለእነርሱ መልካም ነው። ነገር ግን ራሳቸውን መግዛት ካልቻሉ ያግቡ፤ በምኞት ከመቃጠል ማግባት ይሻላልና። ላገቡት ይህን ትእዛዝ እሰጣለሁ፤ ይህም ትእዛዝ የጌታ እንጂ የእኔ አይደለም። ሚስት ከባሏ አትለያይ፤ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር፤ አለዚያ ከባሏ ጋራ ትታረቅ፤ ባልም ሚስቱን አይፍታት። ለሌሎች ደግሞ እንዲህ እላለሁ፤ ይህንም የምለው እኔ እንጂ ጌታ አይደለም። ያላመነች ሚስት ያለው ወንድም ቢኖርና ሚስቱ ዐብራው ለመኖር የምትፈቅድ ከሆነ፣ ሊፈታት አይገባውም። ያላመነ ባል ያላት ሴት ብትኖርና እርሱም ዐብሯት ለመኖር የሚፈቅድ ከሆነ፣ ልትፈታው አይገባትም። ያላመነ ባል በሚስቱ ተቀድሷልና፤ ያላመነችም ሚስት በሚያምን ባሏ ተቀድሳለች፤ አለዚያማ ልጆቻችሁ ርኩሳን በሆኑ ነበር፤ አሁን ግን የተቀደሱ ናቸው። ነገር ግን የማያምነው ወገን መለየት ከፈለገ ይለይ፤ አንድ ወንድም ወይም እኅት በዚህ ሁኔታ የታሰሩ አይደሉም፤ እግዚአብሔር የጠራን በሰላም እንድንኖር ነው። አንቺ ሴት፤ ባልሽን ታድኚው እንደ ሆነ ምን ታውቂያለሽ? ወይስ አንተ ሰው፤ ሚስትህን ታድናት እንደ ሆነ ምን ታውቃለህ? ብቻ እያንዳንዱ ሰው ጌታ እንደ ወሰነለት፣ እያንዳንዱም እግዚአብሔር እንደ ጠራው በዚያው ይመላለስ። በአብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ የምንደነግገው ይህንኑ ነው። አንድ ሰው ተገርዞ ሳለ ቢጠራ፣ እንዳልተገረዘ ሰው አይሁን፤ ሳይገረዝም ተጠርቶ ከሆነ አይገረዝ። መገረዝም ሆነ አለመገረዝ አይጠቅምም፤ ዋናው ነገር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸሙ ነው። እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ሁኔታ ጸንቶ ይኑር። በተጠራህ ጊዜ ባሪያ ነበርህን? በዚህ አትጨነቅ፤ ነጻነትህን ማግኘት ከቻልህ ግን ነጻነትህን ተቀበል። ምክንያቱም ባሪያ ሆኖ ሳለ በጌታ የተጠራ፣ የጌታ ነጻ ሰው ነው፤ እንዲሁም ሲጠራ ነጻ የነበረ ሰው የክርስቶስ ባሪያ ነው። በዋጋ ተገዝታችኋል፤ ስለዚህ የሰው ባሮች አትሁኑ። ወንድሞች ሆይ፤ እያንዳንዱ ሰው በተጠራበት ሁኔታ ከእግዚአብሔር ጋራ ጸንቶ ይኑር። ስለ ደናግል፣ ከጌታ የተቀበልሁት ትእዛዝ የለኝም፤ ይሁን እንጂ፣ ከጌታ ምሕረት የተነሣ እንደ ታማኝ ሰው፣ ምክሬን እሰጣለሁ። አሁን ካለው ችግር የተነሣ ባላችሁበት ሁኔታ ብትኖሩ መልካም ይመስለኛል። አግብተህ ከሆነ መፋታትን አትሻ፤ ካላገባህም ሚስት ለማግባት አትፈልግ። ብታገባ ግን ኀጢአት አልሠራህም፤ ድንግሊቱም ብታገባ ኀጢአት አላደረገችም። ነገር ግን የሚያገቡ ሰዎች በዚህ ዓለም ብዙ ችግር ይገጥማቸዋል፤ እኔም ይህ እንዳይደርስባችሁ እወድዳለሁ። ወንድሞች ሆይ፤ ሐሳቤ እንዲህ ነው፤ ዘመኑ ዐጭር ነው፤ ከእንግዲህ ሚስት ያላቸው እንደሌላቸው ሆነው ይኑሩ። የሚያለቅሱ እንደማያለቅሱ፣ ደስተኞች ደስ እንደማይላቸው ይሁኑ፤ ዕቃ የሚገዙም የገዙት ነገር የእነርሱ እንዳልሆነ ይቍጠሩ፤ በዚህ ዓለም ነገር የሚጠቀሙም እንደማይጠቀሙበት ይሁኑ፤ የዚህ ዓለም መልክ ዐላፊ ነውና። እኔስ ያለ ጭንቀት እንድትኖሩ እወድዳለሁ። ያላገባ ሰው ጌታን ደስ ለማሠኘት ስለ ጌታ ነገር ያስባል፤ ያገባ ሰው ግን ሚስቱን ደስ ለማሠኘት የዚህን ዓለም ነገር ያስባል፤ በዚህም ልቡ ተከፍሏል። ያላገባች ሴት ወይም ድንግል ስለ ጌታ ነገር ታስባለች፤ ዐላማዋም በሥጋና በመንፈስ ለጌታ መቀደስ ነው። ያገባች ሴት ግን ባሏን ደስ ለማሠኘት የዚህን ዓለም ነገር ታስባለች። ይህንም የምለው ለእናንተ የሚበጃችሁን ነገር በማሰብ እንጂ ላስጨንቃችሁ አይደለም፤ ዐላማዬም ልባችሁ ሳይከፈል በጌታ ጸንታችሁ በአግባብ እንድትኖሩ ነው። አንድ ሰው ያጫትን ድንግል በአግባቡ ካልያዘ፣ እርሷም በዕድሜ እየገፋች ከሄደች፣ ሊያገባት ካሰበ የወደደውን ያድርግ፤ ኀጢአት የለበትምና ይጋቡ። ነገር ግን በዚህ ጕዳይ ልቡን አረጋግቶ፣ ሳይናወጥ፣ ራሱንም በመግዛት ድንግሊቱን ላለማግባት የወሰነ ሰው መልካም አድርጓል። ስለዚህ ድንግሊቱን ያገባ መልካም አደረገ፤ ያላገባም የተሻለ አደረገ። አንዲት ሴት ባሏ በሕይወት እስካለ ድረስ ከርሱ ጋራ የታሰረች ናት፤ ባሏ ቢሞት ግን፣ የፈለገችውን ሰው ለማግባት ነጻነት አላት፤ ሰውየው ግን በጌታ መሆን አለበት። እንደ እኔ ከሆነ ግን ሳታገባ እንዲሁ ብትኖር ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለች፤ እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ያለ ይመስለኛል።