1 ቆሮንቶስ 6:1-20

1 ቆሮንቶስ 6:1-20 NASV

ከመካከላችሁ አንድ ሰው ከሌላው ጋራ ሙግት ቢኖረው፣ ጕዳዩን በቅዱሳን ፊት በማቅረብ ፈንታ እንዴት ደፍሮ በዐመፀኞች ፊት ለመፋረድ ያቀርባል? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንደሚፈርዱ አታውቁምን? በዓለም ላይ የምትፈርዱ ከሆነ፣ እንግዲያው፣ በትንሹ ነገር ላይ ለመፍረድ አትበቁምን? በምድራዊ ሕይወት ጕዳይ ቀርቶ፣ በመላእክት ላይ እንኳ እንደምንፈርድ አታውቁምን? እንግዲህ እንዲህ ያለ ጕዳይ ሲያጋጥማችሁ፣ በቤተ ክርስቲያን የተናቁትን ሰዎች ፈራጅ አድርጋችሁ ሹሟ! ይህንም የምለው ላሳፍራችሁ ብዬ ነው። ለመሆኑ በወንድሞች መካከል ለመፍረድ የሚበቃ ጠቢብ ሰው በመካከላችሁ የለምን? ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ለመክሰስ ፍርድ ቤት ይሄዳል፤ ያውም በማያምኑ ሰዎች ፊት! እንግዲህ በመካከላችሁ መካሰስ መኖሩ ራሱ ውድቀታችሁን ያሳያል። ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? እናንተ ግን ራሳችሁ ትበድላላችሁ፤ ታታልላላችሁም፤ ያውም እኮ ወንድሞቻችሁን። ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? በዚህ ነገር አትታለሉ፤ ሴሰኞች፣ ጣዖት አምላኪዎች፣ አመንዝሮች፣ ወንደቃዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣ ወይም ሌቦች፣ ስግብግቦች፣ ሰካራሞች፣ ተሳዳቢዎችና ቀማኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተ አንዳንዶቻችሁ እንደዚህ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋል። “ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤” ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር አይጠቅምም፤ “ሁሉ ነገር ተፈቅዶልኛል፤” ይሁን እንጂ ምንም ነገር በእኔ ላይ አይሠለጥንም። ደግሞም፣ “ምግብ ለሆድ ነው፤ ሆድም ለምግብ ነው፤” እግዚአብሔር ግን ሁለቱንም ያጠፋቸዋል። ሰውነት ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሰውነት ነው። እግዚአብሔር ጌታን ከሙታን እንዳስነሣው፣ እኛንም ደግሞ በኀይሉ ከሙታን ያስነሣናል። ሰውነታችሁ የክርስቶስ የአካሉ ብልቶች እንደ ሆነ አታውቁምን? ታዲያ፣ የክርስቶስን ብልቶች ወስጄ ከዝሙት ዐዳሪ ብልቶች ጋራ አንድ ላድርገውን? ከቶ አይሆንም! ወይስ ከዝሙት ዐዳሪ ጋራ የሚተባበር ሰው ከርሷ ጋራ አንድ ሥጋ እንደሚሆን አታውቁምን? “ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ተብሏልና። ነገር ግን ከጌታ ጋራ የሚተባበር ከርሱ ጋራ አንድ መንፈስ ይሆናል። ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚሠራው ኀጢአት ሁሉ ከአካሉ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚፈጽም ግን በገዛ አካሉ ላይ ኀጢአት ይሠራል። ለመሆኑ፣ ሰውነታችሁ በውስጣችሁ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ይህም መንፈስ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት ነው። እናንተም የራሳችሁ አይደላችሁም፤ በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህ በሰውነታችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።