በመካከላችሁ የዝሙት ርኩሰት እንዳለ በርግጥ ይወራል፤ እንዲህ ያለው ርኩሰት በአረማውያን ዘንድ እንኳ ታይቶ የማይታወቅ ነው፤ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው አለና። ደግሞም ታብያችኋል! ይልቅስ ሐዘን ተሰምቷችሁ፣ ይህን ድርጊት የፈጸመውን ሰው ከመካከላችሁ ልታስወግዱት አይገባምን? ምንም እንኳ እኔ በአካል አብሬያችሁ ባልሆንም፣ በመንፈስ ግን ከእናንተ ጋራ ነኝ፤ ልክ አብሬያችሁ እንዳለሁ ሆኜ፣ ይህን ባደረገው ሰው ላይ አሁኑኑ ፈርጄበታለሁ። በምትሰበሰቡበት ጊዜ እኔም በመንፈስ ከእናንተ ጋራ ስለምሆን፣ በጌታችን በኢየሱስ ስምና በመካከላችሁ በሚገኘው በጌታችን በኢየሱስ ኀይል፣ ሥጋው ጠፍቶ መንፈሱ በጌታ ቀን ትድን ዘንድ፣ እንደዚህ ዐይነቱ ለሰይጣን ይሰጥ። መመካታችሁ መልካም አይደለም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካው አታውቁምን? አሁን ያለ እርሾ እንደ ሆናችሁ ሁሉ አዲስ ሊጥ እንድትሆኑ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ፤ የፋሲካ በጋችን የሆነው ክርስቶስ ተሠውቷልና። ስለዚህ በዓሉን ግፍና ክፋት በሞላበት እርሾ፣ በአሮጌ እርሾ ሳይሆን፣ እርሾ በሌለበት ቂጣ በቅንነትና በእውነት እናክብር። ከሴሰኞች ጋራ እንዳትተባበሩ በመልእክቴ ጽፌላችሁ ነበር፤ እንዲህም ስል በጠቅላላው ከዚህ ዓለም ሴሰኞች ወይም ስግብግቦችና ቀማኞች ወይም ከጣዖት አምላኪዎች ጋራ አትተባበሩ ለማለት አይደለም፤ እንደዚያማ ቢሆን ከዚህ ዓለም ጨርሶ መለየት ያስፈልጋችሁ ነበር። ነገር ግን አሁን የጻፍሁላችሁ፣ “ወንድም ነኝ” እያለ ከሚሴስን ወይም ከሚስገበገብ ወይም ጣዖትን ከሚያመልክ ወይም ከሚሳደብ ወይም ከሚሰክር ወይም ከሚቀማ ጋራ እንዳትተባበሩ ነው፤ ከእንደዚህ ዐይነቱ ሰው ጋራ ምግብ እንኳ አትብሉ። ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ባሉት ሰዎች ላይ ለመፍረድ እኔን ምን አግብቶኝ? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉት ሰዎች ላይ እናንተ አትፈርዱምን? ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ባሉት ላይ የሚፈርድ ግን እግዚአብሔር ነው፤ እንግዲህ፣ “ክፉውን ሰው ከመካከላችሁ አስወግዱት።”
1 ቆሮንቶስ 5 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ቆሮንቶስ 5
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ቆሮንቶስ 5:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች