ወንድሞች ሆይ፤ በክርስቶስ ገና ሕፃናት እንደ መሆናችሁ፣ እንደ ሥጋውያን እንጂ እንደ መንፈሳውያን ልናገራችሁ አልቻልሁም። ገና ስላልጠነከራችሁ ወተት እንጂ ጠንካራ ምግብ አልመገብኋችሁም፤ አሁንም ቢሆን ገና ናችሁ። አሁንም ሥጋውያን ናችሁ፤ በመካከላችሁ ቅናትና ክርክር አለ። ታዲያ፣ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? ተግባራችሁስ እንደ ማንኛውም ሰው ተግባር መሆኑ አይደለምን? ምክንያቱም አንዱ፣ “እኔ የጳውሎስ ነኝ”፣ ሌላው ደግሞ፣ “እኔ የአጵሎስ ነኝ” ቢል፣ ሥጋ ለባሽ ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? ለመሆኑ አጵሎስ ምንድን ነው? ጳውሎስስ ምንድን ነው? ጌታ ለእያንዳንዳቸው በሰጣቸው መጠን የሚሠሩ አገልጋዮች ናቸው፤ እናንተም ወደ እምነት የመጣችሁት በእነርሱ አማካይነት ነው። እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው። ስለዚህ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ፣ የሚተክልም ሆነ ውሃ የሚያጠጣ ምንም አይደለም። የሚተክልም ሆነ የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን የራሱን ሽልማት ይቀበላል። እኛ የእግዚአብሔር የሆንን ዐብሮ ሠራተኞች ነንና፤ እናንተም የእግዚአብሔር ዕርሻ፣ የእግዚአብሔር ሕንጻ ናችሁ። ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ መጠን፣ እንደ አንድ ብልኅ ግንበኛ መሠረትን ጣልሁ፤ ሌላውም በላዩ ላይ ይገነባል፤ ነገር ግን እያንዳንዱ እንዴት እንደሚገነባ መጠንቀቅ አለበት።
1 ቆሮንቶስ 3 ያንብቡ
ያዳምጡ 1 ቆሮንቶስ 3
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1 ቆሮንቶስ 3:1-10
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች