1 ቆሮንቶስ 15:12-34

1 ቆሮንቶስ 15:12-34 NASV

ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፣ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነዋ! ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። ከዚህም በላይ፣ እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በመመስከራችን፣ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣ ክርስቶስንም አላስነሣውም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ሙታን ካልተነሡ፣ ክርስቶስም አልተነሣም። ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢአታችሁ አላችሁ ማለት ነው። እንዲህም ከሆነ፣ በክርስቶስ ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው። ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን። ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በርግጥ ከሙታን ተነሥቷል። ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደ መጣ፣ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኗልና። ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፣ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት። ከዚያም ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፣ ያን ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል፤ ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና፤ የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው። “ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛህለት”፤ ነገር ግን፣ “ሁሉን አስገዛለት” ሲል፣ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጽ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለርሱ ይገዛል። ትንሣኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው? ሙታን ከቶ የማይነሡ ከሆነ፣ ሰዎች ለእነርሱ ብለው ለምን ይጠመቃሉ? እኛስ ብንሆን ዘወትር ለአደጋ የምንጋለጠው ለምንድን ነው? ወንድሞች ሆይ፤ እኔ በየቀኑ እሞታለሁ፤ ይህንም በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክሕት አረጋግጣለሁ። በኤፌሶን ከአራዊት ጋራ የታገልሁት ለሰብኣዊ ተስፋ ብቻ ከሆነ ትርፌ ምንድን ነው? ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣ “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፤ እንጠጣ፤” እንደሚሉት መሆናችን ነው። አትሳቱ፤ “መጥፎ ጓደኛነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል።” ወደ ሰከነ ልቡናችሁ ተመለሱ፤ ኀጢአትንም አትሥሩ፤ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና፤ ይህንም የምለው ላሳፍራችሁ ነው።