1 ቆሮንቶስ 15:1-32

1 ቆሮንቶስ 15:1-32 NASV

አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ የሰበክሁላችሁንና የተቀበላችሁትን፣ ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን ወንጌል ላሳስባችሁ እወድዳለሁ፤ የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣ በዚህ ወንጌል ትድናላችሁ፤ አለዚያ ያመናችሁት በከንቱ ነው። እኔ የተቀበልሁትንና ከሁሉ በላይ የሆነውን ለእናንተ አስተላልፌአለሁ፤ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኀጢአታችን ሞተ፤ ተቀበረ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተጻፈውም በሦስተኛው ቀን ተነሣ፤ ከዚያም ለኬፋ ታየ፤ ቀጥሎም ለዐሥራ ሁለቱ ታየ፤ ከዚያም በኋላ ከዐምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ በሕይወት አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል። ከዚያም ለያዕቆብ ታየ፤ በኋላም ለሐዋርያት በሙሉ ታየ፤ ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምቈጠር ለእኔ ደግሞ ታየ። እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ፣ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ እንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን አሳድጃለሁ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም፤ እንዲያውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋራ ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። እንግዲህ እኔም ሆንሁ እነርሱ የምንሰብከው ይህንኑ ነው፤ እናንተም ያመናችሁት ይህንኑ ነው። ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፣ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነዋ! ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። ከዚህም በላይ፣ እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በመመስከራችን፣ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣ ክርስቶስንም አላስነሣውም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ሙታን ካልተነሡ፣ ክርስቶስም አልተነሣም። ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢአታችሁ አላችሁ ማለት ነው። እንዲህም ከሆነ፣ በክርስቶስ ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው። ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፣ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን። ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በርግጥ ከሙታን ተነሥቷል። ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደ መጣ፣ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኗልና። ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፣ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፣ ከዚያም በኋላ እርሱ ሲመጣ የክርስቶስ የሆኑት። ከዚያም ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፣ ያን ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል፤ ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና፤ የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው። “ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛህለት”፤ ነገር ግን፣ “ሁሉን አስገዛለት” ሲል፣ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጽ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለርሱ ይገዛል። ትንሣኤ ከሌለማ ለሞቱ ሰዎች ብለው የሚጠመቁት ምን እያደረጉ ነው? ሙታን ከቶ የማይነሡ ከሆነ፣ ሰዎች ለእነርሱ ብለው ለምን ይጠመቃሉ? እኛስ ብንሆን ዘወትር ለአደጋ የምንጋለጠው ለምንድን ነው? ወንድሞች ሆይ፤ እኔ በየቀኑ እሞታለሁ፤ ይህንም በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ በእናንተ ላይ ባለኝ ትምክሕት አረጋግጣለሁ። በኤፌሶን ከአራዊት ጋራ የታገልሁት ለሰብኣዊ ተስፋ ብቻ ከሆነ ትርፌ ምንድን ነው? ሙታን የማይነሡ ከሆነ፣ “ነገ ስለምንሞት፣ እንብላ፤ እንጠጣ፤” እንደሚሉት መሆናችን ነው።