1 ቆሮንቶስ 12:12-31

1 ቆሮንቶስ 12:12-31 NASV

አካል ብዙ ብልቶች ቢኖሩትም አንድ አካል ነው፤ ነገር ግን ብልቶች ብዙ ቢሆኑም አካል አንድ ነው። ክርስቶስም እንደዚሁ ነው። አይሁድ ወይም የግሪክ ሰዎች ብንሆን፣ ባሪያ ወይም ነጻ ሰዎች ብንሆን፣ እኛ ሁላችን አንድ አካል እንድንሆን በአንድ መንፈስ ተጠምቀናልና፤ ሁላችንም አንዱን መንፈስ እንድንጠጣ ተሰጥቶናል። አካል የተሠራው ከብዙ ብልቶች እንጂ ከአንድ ብልት አይደለም። እግር፣ “እኔ እጅ ስላልሆንሁ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? ጆሮም፣ “እኔ ዐይን ስላልሆንሁ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? አካል በሙሉ ዐይን ቢሆን ኖሮ፣ መስማት ከየት ይገኝ ነበር? አካል በሙሉ ጆሮ ቢሆን ኖሮ፣ ማሽተት ከየት ይገኝ ነበር? ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ እያንዳንዱን በአካል ውስጥ መድቧል። ሁሉም አንድ ብልት ቢሆን ኖሮ አካል ከየት ይገኝ ነበር? እንግዲህ ብልቶች ብዙ ናቸው፣ አካል ግን አንድ ነው። ዐይን እጅን፣ “አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም፤ ራስም እግርን፣ “አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም። እንዲያውም ደካማ የሚመስሉት የአካል ብልቶች እጅግ አስፈላጊ ናቸው። የተናቁ ለሚመስሉን ብልቶች ይበልጥ ክብር እንሰጣቸዋለን፤ ደግሞም የምናፍርባቸውን ብልቶች ይበልጥ እንንከባከባቸዋለን፤ የማናፍርባቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። እግዚአብሔር ግን የአካል ብልቶችን አንድ ላይ አገጣጥሞ ክብር ለሚጐድላቸው የበለጠ ክብር ሰጥቷቸዋል፤ ይህንም ያደረገው በአካል ብልቶች መካከል መለያየት ሳይኖር፣ እርስ በርሳቸው እኩል እንዲተሳሰቡ ነው። አንድ ብልት ቢሠቃይ፣ ብልቶች ሁሉ ዐብረው ይሠቃያሉ፤ አንድ ብልት ቢከብር፣ ሌሎቹም ብልቶች ዐብረው ደስ ይላቸዋል። እንግዲህ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ብልቶች ናችሁ። እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንደኛ ሐዋርያትን፣ ሁለተኛ ነቢያትን፣ ሦስተኛ መምህራንን፣ ቀጥሎም ታምራት አድራጊዎችን፣ የመፈወስ ስጦታዎች ያላቸውን፣ ሌሎችን የመርዳት ስጦታ ያላቸውን፣ የማስተዳደር ስጦታ ያላቸውንና በልዩ ልዩ ልሳን የመናገር ስጦታ ያላቸውን ሰዎች መድቧል። ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን? ሁሉስ መምህራን ናቸውን? ሁሉስ ታምራት ያደርጋሉን? ሁሉስ የመፈወስ ስጦታዎች አላቸውን? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን? ሁሉስ ይተረጕማሉን? ነገር ግን ከሁሉ የሚበልጠውን ስጦታ በብርቱ ፈልጉ።