1 ቆሮንቶስ 10:1-22

1 ቆሮንቶስ 10:1-22 NASV

ወንድሞች ሆይ፤ አባቶቻችን ሁሉ ከደመናው በታች እንደ ነበሩና በባሕሩ ውስጥ እንደ ተሻገሩ ታውቁ ዘንድ እፈልጋለሁ። እነርሱ ሁሉ ከሙሴ ጋራ ለመተባበር በደመናና በባሕር ተጠመቁ። ሁሉም ከአንድ መንፈሳዊ ምግብ በሉ፤ ሁሉም ከአንድ መንፈሳዊ መጠጥ ጠጡ፤ ይከተላቸው ከነበረው መንፈሳዊ ዐለት ጠጥተዋልና፤ ያ ዐለት ክርስቶስ ነበረ። ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በብዙዎቹ ደስ ስላልተሠኘ በበረሓ ወድቀው ቀሩ። እነርሱ ክፉ እንደ ተመኙ፣ እኛም ደግሞ እንዳንመኝ እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ሆነውልናል። “ሕዝቡ ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ” ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖት አምላኪዎች አትሁኑ። ከእነርሱ አንዳንዶቹ ዝሙት ፈጽመው በአንድ ቀን ሃያ ሦስት ሺሕ ሰው እንደ ረገፈ፣ እኛም ዝሙት አንፈጽም። ከእነርሱ አንዳንዶቹ ጌታን እንደ ተፈታተኑና በእባብ ተነድፈው እንደ ጠፉ፣ እኛም ጌታን አንፈታተን። ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳጕረመረሙና በአጥፊው እንደ ጠፉ፣ አታጕረምርሙ። ይህ ሁሉ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በእነርሱ ላይ ደረሰ፤ የዘመናት ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅም ተጻፈ። ስለዚህ ተደላድዬ ቆሜአለሁ የሚል ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። በሰዎች ሁሉ ላይ ከደረሰው የተለየ ፈተና አልደረሰባችሁም፤ እግዚአብሔር ታማኝ ነው፤ ስለዚህ ከምትችሉት በላይ እንድትፈተኑ አይተዋችሁም፤ ነገር ግን በምትፈተኑበት ጊዜ ፈተናውን መታገሥ እንድትችሉ፣ መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል። ስለዚህ ወዳጆቼ ሆይ፤ ከጣዖት አምልኮ ሽሹ። ይህን የምናገረው አስተዋይ ለሆኑ ሰዎች ነው፤ ስለምናገረው ነገር እናንተው ፍረዱ። የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋራ ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋራ ኅብረት ያለው አይደለምን? እንጀራው አንድ እንደ ሆነ፣ እኛም ብዙዎች ሆነን ሳለ አንድ አካል ነን፤ ሁላችን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና። እስኪ የእስራኤልን ሕዝብ አስቡ፤ መሥዋዕቱን የሚበሉት ከመሠዊያው ጋራ ኅብረት አልነበራቸውምን? ታዲያ፣ ለጣዖት የተሠዋ ነገርም ሆነ ጣዖቱ ራሱ ዋጋ ያለው ነገር ነው ማለቴ ነውን? አይደለም፤ አሕዛብ የሚሠዉት ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለአጋንንት ነው፤ ከአጋንንት ጋራ እንድትተባበሩም አልሻም። የጌታን ጽዋና፣ የአጋንንትን ጽዋ በአንድ ላይ መጠጣት አትችሉም፤ ከጌታ ማእድና ከአጋንንት ማእድ ተካፋይ መሆን አትችሉም። ጌታን እናስቀናውን? በብርታትስ ከርሱ እንበልጣለንን?