እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስ መጣ፥ በዙሪያው ብርሃን ያለው መብረቅን የሚረጭ ታላቅ ደመና ነበር፥ በእሳቱም መካከል የሚያንጸባርቅ ነገር ነበረ። ከመካከልም አራት ሕያው ፍጡራን የሚመስሉ ወጡ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፥ ሰውም ይመስሉ ነበር። እያንዳንዳቸውም አራት ፊቶች፥ እያንዳንዳቸውም አራት ክንፎች ነበራቸው። እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ እግሮች ነበሩ፥ የእግሮቻቸውም ኮቴ እንደ ጥጃ እግር ኮቴ ነበረ፥ እንደ ተወለወለ ናስም ያንጸባርቅ ነበር። ከክንፎቻቸውም ስር በአራቱም ጎናቸው የሰው እጆች ነበሩ፤ አራቱም ፊቶቻቸውና ክንፎቻቸው እንዲህ ነበሩ፦ ክንፎቻቸው እርስ በእርሱ ይነካካ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም፥ እያንዳንዱም ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር።