ሕዝቅኤል 1:4-9
ሕዝቅኤል 1:4-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እኔም አየሁ፤ እነሆም ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና፥ የሚበርቅም እሳት መጣ፤ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ፤ በመካከልም በእሳቱ ውስጥ የሚብለጨለጭ ነገር ነበረ። ከመካከልም የአራት እንስሶች አምሳያ ወጣ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፤ ሰውም ይመስሉ ነበረ። ለእያንዳንዱም አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት። እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ ነበሩ፤ የእግራቸው ሰኰና እንደ ላም እግር ሰኰና ነበረ፤ እንደ ተወለወለ ናስም ይብለጨለጭ ነበር። በክንፎቻቸውም በታች በእየአራቱ ጐድናቸው የሰው እጅ ነበረ፤ ለአራቱም እንደዚህ ያሉ ፊትና ክንፍ ነበሩአቸው። የሁሉም ክንፎቻቸው አንዱ ከአንዱ ጋር የተያያዘ ነው፤ ሲሄዱም ወዲያና ወዲህ ሳይሉ አቅንተው ይሄዳሉ፤ አንዱም አንዱም ወደፊቱ ይሄዳል።
ሕዝቅኤል 1:4-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እኔም አየሁ፤ ስመለከትም፣ እነሆ ዐውሎ ነፋስ ከሰሜን በኩል መጣ፤ ይኸውም በታላቅ ብርሃን የተከበበ፣ መብረቅን የሚረጭ ታላቅ ደመና ነበረ፤ የእሳቱም መኻል የጋለ ብረት ይመስል ነበር። በእሳቱም ውስጥ የአራት ሕያዋን ፍጡራን አምሳያ ነበረ፤ መልካቸውም የሰው ቅርጽ ይመስል ነበር። እያንዳንዳቸውም አራት አራት ፊትና አራት አራት ክንፍ ነበራቸው። እግራቸው ቀጥ ያለ ነበር፤ ኰቴያቸውም እንደ ጥጃ ኰቴ ያለ ሲሆን፣ እንደ ተወለወለ ናስም ያብለጨልጭ ነበር። በአራቱ ጐኖቻቸው ባሉት ክንፎቻቸው ሥር የሰው እጅ ነበራቸው። አራቱም ፊቶችና ክንፎች ነበሯቸው፤ ክንፎቻቸውም እርስ በርስ ይነካኩ ነበር። እያንዳንዱም ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር፤ ወደ ኋላቸውም ዞር ብለው አይመለከቱም ነበር።
ሕዝቅኤል 1:4-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስና ታላቅ ደመና የሚበርቅም እሳት መጣ፥ በዙሪያውም ፀዳል ነበረ፥ በመካከልም በእሳቱ ውስጥ እንደሚብለጨለጭ የወርቅ ምስያ ነበረ። ከመካከልም የአራት እንስሶች አምሳያ ወጣ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፥ ሰውም ይመስሉ ነበር። ለእያዳንዱም አራት አራት ፊት፥ ለእያንዳንዱም አራት አራት ክንፍ ነበሩት። እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ እግሮች ነበሩ፥ የእግራቸውም ኮቴ እንደ ጥጃ እግር ኮቴ ነበረ፥ እንደ ተወለወለ ናስም ይብለጨለጭ ነበር። በክንፎቻቸውም በታች በእያራቱ ጐድናቸው እንደ ሰው እጅ ነበረ፥ ለአራቱም እንደዚህ ያሉ ፊትና ክንፍ ነበሩአቸው። ክንፎቻቸው እርስ በእርሱ የተያያዘ ነበረ፥ ሲሄዱም አይገላምጡም ነበረ፥ እያንዳንዱም ፊቱን አቅንቶ ይሄድ ነበር።
ሕዝቅኤል 1:4-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀና ብዬ ስመለከት ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ከሰሜን በኩል ሲመጣ አየሁ፤ ከግዙፍ ደመና የመብረቅ ብልጭታ ይታይ ነበር፤ በዙሪያው ያለውም ሰማይ ቀላ፤ መብረቁ በሚበርቅበትም ስፍራ አንዳች ነገር እንደ ነሐስ አበራ። በዐውሎ ነፋሱም መካከል የሰው መልክ ያላቸው አራት ሕያዋን ፍጥረቶች አየሁ፤ እያንዳንዱም ፍጥረት አራት አራት ፊትና አራት አራት ክንፍ ነበሩት። እግራቸው ቀጥ ያለ ሲሆን፥ ውስጥ እግራቸው እንደ ኰርማ ሰኮና ነበር፤ መልካቸውም እንደ ተወለወለ ነሐስ ያበራ ነበር፤ ከአራቱ ፊቶቻቸውና ከአራቱ ክንፎቻቸው ሌላ እያንዳንዳቸው ከክንፎቻቸው ግርጌ አራት የሰው ዐይነት እጆች ነበሩአቸው። የእያንዳንዱ ፍጥረት ሁለት ክንፎች ግራና ቀኝ ተዘርግተው ጫፎቻቸው ይነካካሉ፤ ስለዚህ ሰውነታቸው ወዲያና ወዲህ ሳይል በኅብረት ይንቀሳቀሱ ነበር።
ሕዝቅኤል 1:4-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እኔም አየሁ፥ እነሆም፥ ከሰሜን በኩል ዐውሎ ነፋስ መጣ፥ በዙሪያው ብርሃን ያለው መብረቅን የሚረጭ ታላቅ ደመና ነበር፥ በእሳቱም መካከል የሚያንጸባርቅ ነገር ነበረ። ከመካከልም አራት ሕያው ፍጡራን የሚመስሉ ወጡ። መልካቸውም እንደዚህ ነበረ፥ ሰውም ይመስሉ ነበር። እያንዳንዳቸውም አራት ፊቶች፥ እያንዳንዳቸውም አራት ክንፎች ነበራቸው። እግሮቻቸውም ቀጥ ያሉ እግሮች ነበሩ፥ የእግሮቻቸውም ኮቴ እንደ ጥጃ እግር ኮቴ ነበረ፥ እንደ ተወለወለ ናስም ያንጸባርቅ ነበር። ከክንፎቻቸውም ስር በአራቱም ጎናቸው የሰው እጆች ነበሩ፤ አራቱም ፊቶቻቸውና ክንፎቻቸው እንዲህ ነበሩ፦ ክንፎቻቸው እርስ በእርሱ ይነካካ ነበር፥ ሲሄዱም አይዞሩም፥ እያንዳንዱም ቀጥ ብሎ ይሄድ ነበር።