ማቴዎስ 4
4
የኢየሱስ መፈተን
4፥1-11 ተጓ ምብ – ማር 1፥12-13፤ ሉቃ 4፥1-13
1ከዚህ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን በዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። 2አርባ ቀን እና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ። 3ፈታኙም ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፣ እነዚህን ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው።
4ኢየሱስም፣ “ ‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል”#4፥4 ዘዳ 8፥3 ሲል መለሰለት።
5ቀጥሎም ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ቅድስት ከተማ በመውሰድ ከቤተ መቅደሱም ዐናት ላይ አውጥቶ፣ 6“የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ራስህን ወደ መሬት ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤
“ ‘መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል፣
እግርህም ከድንጋይ ጋራ እንዳይጋጭ፣
በእጆቻቸው ያነሡሃል።’#4፥6 መዝ 91፥11-12”
7ኢየሱስም፣ “እንደዚሁም በመጻሕፍት፣ ‘ጌታ አምላክህን አትፈታተነው’#4፥7 ዘዳ 6፥16 ተብሎ ተጽፏል” ብሎ መለሰለት።
8እንደ ገናም ዲያብሎስ ኢየሱስን እጅግ ከፍ ወዳለ ተራራ አወጣው፤ የዓለምን መንግሥታት ከነክብራቸው አሳየውና፣ 9“ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው።
10ኢየሱስም፣ “አንተ ሰይጣን ከፊቴ ራቅ! ‘ለጌታ ለአምላክህ ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’#4፥10 ዘዳ 6፥13 ተብሎ ተጽፏል” አለው።
11ከዚያም ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፤ መላእክትም መጥተው አገለገሉት።
ኢየሱስ ስብከት መጀመሩ
12ኢየሱስ የዮሐንስን መታሰር በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ተመለሰ። 13የናዝሬትንም ከተማ ትቶ፣ በዛብሎንና በንፍታሌም አካባቢ በባሕሩ አጠገብ በምትገኘው በቅፍርናሆም ከተማ ሄዶ መኖር ጀመረ። 14በዚህም በነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፤
15“የዛብሎን ምድር፣ የንፍታሌም ምድር፣
ከዮርዳኖስ ማዶ በባሕር መንገድ አጠገብ፣
ያለው የአሕዛብ ገሊላ፣
16በጨለማ የሚኖር ሕዝብ
ታላቅ ብርሃን አየ፤
በሞት ጥላ ምድር ላሉት
ብርሃን ወጣላቸው።”#4፥16 ኢሳ 9፥1-2
17ከዚያ ጊዜ አንሥቶ ኢየሱስ፣ “ንስሓ ግቡ፤ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና” እያለ መስበክ ጀመረ።
የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት መጠራት
4፥18-22 ተጓ ምብ – ማር 1፥16-20፤ ሉቃ 5፥2-11፤ ዮሐ 1፥35-42
18ኢየሱስ በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲያልፍ፣ ሁለት ወንድማማቾች ማለትም፣ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንንና ወንድሙን እንድርያስን አያቸው። ዓሣ አጥማጆች ነበሩና መረባቸውን ወደ ባሕሩ ይጥሉ ነበር። 19ኢየሱስም፣ “ኑ፣ ተከተሉኝ፤ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ” አላቸው። 20ወዲያው መረባቸውን ትተው ተከተሉት።
21ዐለፍ እንዳለም፣ ሌሎች ሁለት ወንድማማቾች፣ የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብንና ወንድሙን ዮሐንስን አየ። ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋራ በጀልባ ሆነው መረባቸውን ያበጁ ነበር። ኢየሱስም ጠራቸው፤ 22ወዲያውኑ ጀልባቸውንም ሆነ አባታቸውን ትተው ተከተሉት።
የበሽተኞች መፈወስ
23ኢየሱስም በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ፣ በሕዝቡ መካከል ማንኛውንም ደዌና ሕመም እየፈወሰ በመላው ገሊላ ይዘዋወር ነበር። 24ከዚህም የተነሣ ዝናው በመላዋ ሶርያ ተሰማ፤ ሕዝቡም በተለያዩ በሽታዎች የታመሙትን፣ በክፉ ደዌ የሚሠቃዩትን፣ አጋንንት ያደሩባቸውን፣ የሚጥል በሽታ ያለባቸውን፣ ሽባዎችን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ ፈወሳቸውም። 25ከዚህም የተነሣ ከገሊላ፣ ከ “ዐሥር ከተማ”፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ማዶ የመጡ ብዙ ሰዎች ተከተሉት።
موجودہ انتخاب:
ማቴዎስ 4: NASV
سرخی
کاپی
موازنہ
شئیر
کیا آپ جاہتے ہیں کہ آپ کی سرکیاں آپ کی devices پر محفوظ ہوں؟ Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.