ኦሪት ዘፍጥረት 1

1
የዓለም አፈጣጠር ታሪክ
1በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ። 2በዚያን ጊዜ ምድር ቅርጽ የሌላትና ባዶ ነበረች፤ ጨለማም በጥልቁ (ውቅያኖስ) ላይ ነበር፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውሃው ላይ ይሰፍ ነበር።
3ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ብርሃን ይሁን” አለ፤ ብርሃንም ሆነ። #2ቆሮ. 4፥6። 4እግዚአብሔርም፥ ብርሃን መልካም መሆኑን አየ፤ እግዚአብሔርም ብርሃንን ከጨለማ ለየ። 5እግዚአብሔር ብርሃኑን “ቀን” ብሎ ጠራው፤ ጨለማውንም “ሌሊት” ብሎ ሰየመው። ቀኑ መሸ፤ ሌሊቱም ነጋ፤ ይህም አንድ ቀን ሆነ።
6ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ውሃውን ከውሃ የሚለይ ጠፈር ይሁን” አለ፤ 7በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር ጠፈርን ፈጠረ፤ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር “ከጠፈር በታችና ከጠፈር በላይ ያሉት ውሆች ይለያዩ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። 8እግዚአብሔር ጠፈርን “ሰማይ” ብሎ ጠራው። ቀኑ መሸ፥ ሌሊቱም ነጋ፤ ሁለተኛ ቀን ሆነ። #2ጴጥ. 3፥5።
9ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “የብሱ ግልጥ ሆኖ እንዲታይ ከሰማይ በታች ያለው ውሃ ሁሉ በአንድ ስፍራ ይሰብሰብ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። 10የብሱን “ምድር” ብሎ ጠራው፤ በአንድ ስፍራ የተሰበሰበውንም ውሃ “ባሕር” ብሎ ሰየመው፤ እግዚአብሔርም ይህ መልካም መሆኑን አየ። 11ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ምድር አትክልትን፥ የእህል አዝርዕትን፥ ፍሬ የሚያፈሩ የፍሬ ዛፎችንና ተክሎችን በየዐይነቱ ታብቅል” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። 12በዚህ ዐይነት ምድር አትክልትን፥ በየዐይነቱ የእህል አዝርዕትንና ዘር በውስጡ ያለውን ፍራፍሬ የሚያስገኙ ተክሎችን አበቀለች፤ እግዚአብሔርም ይህ መልካም መሆኑን አየ። 13ቀኑ መሸ፤ ሌሊቱም ነጋ፤ ሦስተኛ ቀን ሆነ።
14ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ቀንን ከሌሊት ለመለየት ልዩ ልዩ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ላይ ይሁኑ፤ ለዕለታት፥ ለክፍላተ ዓመትና ለዓመታት መለያ ምልክት ይሁኑ፤ 15ለምድር ብርሃን ለመስጠት በሰማይ ጠፈር ላይ ሆነው ያብሩ” እንዲሁም ሆነ። 16በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር ሁለት ታላላቅ ብርሃናትን ፈጠረ፤ ታላቁ ብርሃን በቀን፥ ታናሹ ብርሃን በሌሊት እንዲያበሩ አደረገ፤ እንዲሁም ከዋክብትን ፈጠረ፤ 17ለምድር ብርሃንን እንዲሰጡ እነዚህን ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ላይ አኖራቸው፤ 18ይህንንም ያደረገው በቀንና በሌሊት ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸውና ጨለማን ከብርሃን እንዲለዩ ነው። እግዚአብሔርም ይህ መልካም መሆኑን አየ። 19ቀኑ መሸ፤ ሌሊቱም ነጋ፤ አራተኛ ቀን ሆነ።
20ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ውሃ ሕይወት ባላቸው በልዩ ልዩ ፍጥረቶች የተሞላ ይሁን፤ ወፎችም ከምድር በላይ ባለው በሰማይ ጠፈር ይብረሩ” አለ። 21በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር ታላላቅ የባሕር አውሬዎችን፥ ሌሎችንም በውሃ ውስጥ የሚኖሩና የሚንቀሳቀሱ ልዩ ልዩ ፍጥረቶችን እንደየዐይነታቸው፥ እንዲሁም ልዩ ልዩ ወፎችን እንደየዐይነታቸው ፈጠረ። እግዚአብሔርም ይህ መልካም መሆኑን አየ። 22እግዚአብሔር “ብዙ ተባዙ፤ ዘራችሁ የባሕርን ውሃ ይሙላ፤ ወፎችም በምድር ላይ ይብዙ” ብሎ ባረካቸው። 23ቀኑ መሸ፤ ሌሊቱም ነጋ፤ አምስተኛ ቀን ሆነ።
24ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ምድር ሕይወት ያላቸው ፍጥረቶችን፥ እንደየዐይነታቸው እንስሶችን፥ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችንና አራዊትን እንደየዐይነታቸው ታስገኝ” አለ፤ እንዲሁም ሆነ። 25በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር የምድር አራዊትን በየዐይነቱ፥ እንስሶችን በየዐይነታቸው በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችን በየዐይነታቸው ፈጠረ። እግዚአብሔርም ይህ መልካም መሆኑን አየ።
26ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር “ሰውን በመልካችንና በአምሳያችን እንፍጠር፤ ሰዎችም በባሕር ውስጥ በሚኖሩ ዓሣዎች፥ በሰማይ በሚበርሩ ወፎች፥ በእንስሶችና በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ በሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች፥ እንዲሁም በምድር ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ። #1ቆሮ. 11፥7።
27በዚህ ዐይነት እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎም ፈጠራቸው። #ማቴ. 19፥4፤ ማር. 10፥6። 28እግዚአብሔርም “ብዙ፤ ተባዙ፤ ዘራችሁ ምድርን ይሙላ፤ ምድርም በቊጥጥራችሁ ሥር ትሁን፤ በባሕር ውስጥ በሚኖሩ ዓሣዎች፥ በሰማይ በሚበርሩ ወፎችና በምድር ላይ በሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራችሁ” ብሎ ባረካቸው። #ዘፍ. 5፥1-2። 29እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ምግብ እንዲሆኑአችሁ በምድር ገጽ ላይ የሚገኙትን የእህል አዝርዕትንና ዘር በውስጡ ያለውን ፍራፍሬ የሚያስገኙ ተክሎችን ሁሉ ሰጥቻችኋለሁ። 30እንዲሁም በምድር ላይ ለሚኖሩ እንስሶች ሁሉ፥ በሰማይ ለሚበርሩ ወፎች ሁሉ፥ በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ ለሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች ሁሉ፥ በአጠቃላይ የሕይወት እስትንፋስ ላለው ፍጥረት ሁሉ ምግብ እንዲሆናቸው ልምላሜ ያለውን ሣርና ቅጠል ሁሉ ሰጥቻቸዋለሁ።” እንዲሁም ሆነ። 31እግዚአብሔር የፈጠረውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፥ እጅግ መልካም ነበረ። ቀኑ መሸ፤ ሌሊቱ ነጋ፤ ስድስተኛ ቀን ሆነ።

Выделить

Поделиться

Копировать

None

Хотите, чтобы то, что вы выделили, сохранялось на всех ваших устройствах? Зарегистрируйтесь или авторизуйтесь

YouVersion использует файлы cookie, чтобы персонализировать ваше использование приложения. Используя наш веб-сайт, вы принимаете использование нами файлов cookie, как описано в нашей Политике конфиденциальности