ዘፀአት 1
1
እስራኤላውያን በጭቈና ሥር
1ቤተ ሰቦቻቸውን ይዘው ከያዕቆብ ጋራ ወደ ግብጽ የሄዱት የእስራኤል ልጆች ስሞች እነዚህ ናቸው፦
2ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣
3ይሳኮር፣ ዛብሎን፣ ብንያም፣
4ዳን፣ ንፍታሌም፣
ጋድና አሴር።
5የያዕቆብ ዘር ጠቅላላ ብዛት ሰባ#1፥5 የማሶሬቱ ቅጅ (ዘፍ 46፥27 ይመ)፣ የሙት ባሕር ጥቅልል እንዲሁም የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም (ሐሥ 7፥14 እና የዘፍ 46፥27 ማብ ይመ)፣ ሰባ ዐምስት ይላሉ። ሲሆን፣ ዮሴፍ ግን ቀደም ብሎ በግብጽ ነበረ።
6ከጊዜ በኋላ ዮሴፍና ወንድሞቹ ያም ትውልድ በሙሉ ሞቱ፤ 7ይሁን እንጂ እስራኤላውያን እየተዋለዱ በዙ፤ ቍጥራቸው እጅግ ከመጨመሩም የተነሣ የግብጽን ምድር ሞሏት።
8በግብጽም፣ ስለ ዮሴፍ የማያውቅ አዲስ ንጉሥ ነገሠ። 9እርሱም ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ እስራኤላውያን በቍጥር በልጠውናል፤ ከእኛም ይልቅ እየበረቱ ነው፤ 10ቍጥራቸው እንዳይጨምር፣ ጦርነት ቢነሣ ከጠላቶቻችን ጋራ ዐብረው እንዳይወጉንና ከምድሪቱም ኰብልለው እንዳይሄዱ ዘዴ እንፈልግ።”
11ስለዚህ እያስጨነቁ የግዳጅ ሥራ የሚያሠሯቸውን አሠሪ አለቆች ሾሙባቸው። እስራኤላውያንም ፊቶምና ራምሴ የተባሉ ንብረት ማከማቻ ከተሞችን ለፈርዖን ሠሩለት። 12ነገር ግን ባስጨነቋቸው መጠን የእስራኤላውያን ቍጥር በዛ፤ በምድሪቱም እየተስፋፉ ሄዱ፤ ከዚህም የተነሣ ግብጻውያኑ እስራኤላውያንን እጅግ ፈሯቸው፤ 13ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታም ያሠሯቸው ጀመር። 14ጭቃ በማስቦካት፣ ጡብ በማሠራትና በዕርሻም ሁሉ እያስጨነቁ ከባድ ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ ሕይወታቸውን አስመረሩ፤ ግብጻውያኑ በሚያሠሯቸው ከባድ ሥራ ሁሉ ፈጽሞ አይራሩላቸውም ነበር።
15የግብጽም ንጉሥ ሲፓራና ፉሐ የተባሉትን ዕብራውያን ሴቶች አዋላጆች እንዲህ አላቸው፤ 16“የዕብራውያንን ሴቶች በማማጫው ድንጋይ ላይ በምታዋልዱበት ጊዜ የሚወለደው ሕፃን ወንድ ከሆነ ግደሉት፤ ሴት ከሆነች ግን በሕይወት ትኑር።” 17አዋላጆቹ ግን እግዚአብሔርን ስለ ፈሩ የግብጽ ንጉሥ ያዘዛቸውን አልፈጸሙም፤ ወንዶቹንም ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ ተዉአቸው። 18ንጉሡም አዋላጆቹን ጠርቶ፣ “ለምንድን ነው ወንዶቹን ልጆች በሕይወት እንዲኖሩ የተዋችኋቸው?” አላቸው።
19እነርሱም፣ “የዕብራውያን ሴቶች እንደ ግብጻውያን ሴቶች አይደሉም፤ ብርቱዎች ስለ ሆኑ አዋላጆች ከመድረሳቸው በፊት ይወልዳሉ” ሲሉ ለፈርዖን መለሱለት።
20ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ለአዋላጆቹ መልካም ሆነላቸው፤ ሕዝቡም በቍጥር እየበዛና እያየለ ሄደ። 21አዋላጆቹም እግዚአብሔርን በመፍራታቸው ቤተ ሰብ ሰጣቸው።
22ፈርዖንም፣ “የሚወለደውን ወንድ ልጅ#1፥22 የማሶሬቱ ቅጅ፣ ኦሪተ ሳምራውያን፣ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም እንዲሁም ታርጕም ከዕብራውያን የሚወለደውን ይላሉ። ሁሉ አባይ ወንዝ ውስጥ ጣሉት፤ ሴት ልጅ ሁሉ ግን በሕይወት ትኑር” ሲል ሕዝቡን አዘዘ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.